የኢትዮጵያ ቆይታችን የ'በቃ' ዘመቻውን ይበልጥ ለማቀጣጠል ይረዳናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቆይታችን የ'በቃ' ዘመቻውን ይበልጥ ለማቀጣጠል ይረዳናል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 22/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቆይታችን የ'በቃ' ዘመቻውን የበለጠ ለማቀጣጠል የሚረዳን ነው ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዳያስፖራዎች ገለጹ።
አቶ ደረጀ ደስታ በእንግሊዝ ለንደን ከ30 ዓመታት በላይ ኖረዋል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው በኢትዮጵያ ተገኝተዋል።
ባለፉት ዓመታት የነበረው ሥርዓት የአገሬን መሬት እንዳልረግጥ አድርጎኝ ቆይቷል ያሉት አቶ ደረጀ አገሬን በማየቴ ዳግም የተወለድኩ ያህል ተሰምቶኛል ሲሉ ነው የገለጹት።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው እየጎበኙ መሆኑን፤ ኢትዮጵያ ሠላማዊና የእድገት ጉዞ ላይ መሆኗን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
የ'በቃ' /#.NoMore/ እንቅስቃሴን የበለጠ ለመግፋት ተጨማሪ አቅም የሚሆንና የሚያኮራ ነገር አይተናል በቀጣይም ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
ምዕራባዊያን የኢትዮጵያን እውነታ እየካዱ ሠላም የለም ቢሉም አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ መምጣቱ እውነታውን ለዓለም ያሳያል ነው ያሉት።
አዲስ አበባ ሠላም መሆኗን፣ ሕዝቡ ሰርቶ እንደሚኖር በአካል መጥተው የሚያዩ ነጮችም ምስክር መሆን የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው እኛም ትግሉን እንድንቀጥል የሚያደርገን ነው ብለዋል።
ከአሜሪካ ኢንዲያና ስቴት የመጡት አቶ ሞገስ አባተ በበኩላቸው ወደ አገር ቤት ያልመጡ ኢትዮጵያዊያን በቂ መረጃ ላይኖራቸው ስለሚችል ይህን በማስረዳት በአገራቸው ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ዳያስፖራው ያሳየውን አንድነትና ኅብረት እንዲሁም መነቃቃት መንግስት ሊጠቀምበት ይገባል ያሉት ደግሞ አቶ ዮናስ ሳቀታ ናቸው።