በክልሉ በከፊል ስራ አቁመው የቆዩ ፍርድ ቤቶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

42

ባህር ዳር ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በህልውና ዘመቻው ምክንያት ከአንድ ወር ተኩል በላይ በከፊል አገልግሎት አቋርጠው የቆዩ ፍርድ ቤቶች የተሟላ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።

አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው 7 የክልሉ ዞኖች በ61 ፍርድ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱም ተገልጿል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚደንት አቶ አብዬ ካሳሁን ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሃት ቡድን  በክልሉ በፈፀመው ወረራ ህዝብን በማጎሳቆል ለከፋ ችግርና እንግልት ዳርጎ ቆይቷል።  

ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ መንግስት የአሸባሪውን ቡድን ወረራ በሙሉ አቅም ለመመከት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት በማድረግ ከህዳር 1/2014 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 17/2014 ዓ/ም ድረስ በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቶች የፍትሃ ብሄር ጉዳዮችን ማየት በማቆም የወንጀልና አጣዳፊ ጉዳዮችን ብቻ ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ሁሉም ተቋማት ተቋርጦ የቆየውን ስራ እንዲጀምሩ በክልሉ መንግስት መወሰኑን ተከትሎ ፍርድ ቤቶችም ከታህሳስ 18/2014 ጀምሮ በተሟላ ሁኔታ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አስረድተዋል።  

ፍትህ ፈላጊው ህብረተሰብም በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አቋርጠው የቆዩትን አገልግሎት በሙሉ አቅማቸው የጀመሩ መሆናቸውን አውቆ ጉዳዩን ቀርቦ እንዲከታተል ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።  

በየደረጃው የሚገኙ ዳኞች፣ ሰራተኞችና አመራሮችም በመደበኛ ስራቸው ላይ ተገኝተው ለህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ከነበረው ስራ በበለጠ በመስራት ለህዝቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጡ አሳስበዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ አሸባሪ ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው 7 ዞኖች ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች እስከ ንዑስ ወረዳ በሚገኙ 61 ፍርድ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

ንብረቶችን ዘርፏል፤ የቀረውን አገልግሎት እንዳይሰጥ አውድሟል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የደንበኞችን ፋይሎች በማቃጠልና አገልግሎት እንዳይሰጡ አድርጎ በማውደም እኩይ ተግባር መፈጸሙን አመልክተዋል።

የወደሙና ጉዳት የደረሰባቸውን ፍርድ ቤቶች ወደ ቀደመ አገልግሎታቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

አስቸጋሪ ከሚባሉ የባልና ሚስት፣ የአሰሪና ሰራተኛ፣ የወንጀል ጉዳዮች በስተቀር መደበኛ የሆኑ የፍትሃ ብሄር አገልግሎቶች ተቋርጠው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ፍስሃ ሲሳይ ናቸው።

"ፍርድ ቤቶች ወደ ቀደመ መደበኛ ስራቸው መመለሳቸው ከፍትህ ፈላጊው የህብረተሰብ ክፍል በተጨማሪ እኛም ያቋረጥናቸውን ክርክሮች እንድናስቀጥል ያስችለናል" ብለዋል።

"በህልውና ዘመቻው ተዘግተው የነበሩ ፍርድ ቤቶች  አሁን ላይ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ተገቢ ነው" ያሉት ደግሞ ከደቡብ አቸፈር ወረዳ የመጡት ባለጉዳይ አቶ ተማረ ሞላ ናቸው። ።

ከደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የመጡ ተገልጋይ አቶ አለባቸው መለሰ በበኩላቸው  ፍርድ ቤቶች ስራ በመጀመራቸው  ጉዳያቸው በአጭር ጊዜ ውሳኔ ያገኛል ብለው እንደሚያምኑ አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም