የአገሪቷ ዓለም አቀፍ ውክልና እንዲጎላ እየተሰራ ነው-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

3164
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 ኢትዮጵያ አሁን በዓለም ካላት የፖለቲካና ዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንዲሁም ተሰሚነትና ተደማጭነት ረገድ ያላትን ውክልና ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለሰ ዓለም በዚሁ ወቅት እንደተናሩት በሁለተኛው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እንዲከፈቱ ከተያዙ ሚሲዮኖች መካከል በሞሮኮ፣ በአልጄርያና በሩዋንዳ ኤምባሲዎችን፤ እንዲሁም በቱሪክ ኢስታምቡል ቆንስላ ጄነራል መክፈት ተችሏል። በቀጣይ  በርካታ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በእስያና ኦሺኒያ እንዲሁም በመካክለኛው ምስራቅ አገራት ለመክፈት መታቀዱንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። ይህም ውክልናን ለማስፋት፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን ለማሳደግ፣ የዜጎችን መብት ለማስከበር፣ የኢንቨስትመንት፣ የቱሪዝም፣ የገጽታ ግንባታ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው የጠቀሱት፡፡ በኢህአዴግ በኩል የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም ለአገሪቱ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ መዳበር የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አቶ መለሰ አብራርተዋል። የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች በቅርቡ በአዲስ አበባ የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት ማሳለጫ መድረክ እንዲተገበር ኢጋድና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግፊቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫው ተጠቁሟል። ለሰላም ስምምነቱ መተግበር በዋና ዋና ተቀናቃኞች በኩል ቁርጠኝነት መኖሩን የገለጹት አቶ መለስ አንዳንድ ቦታዎች የሚታዩ ውጥረቶች ተፈተው ተግባራዊነቱ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም