ዳያስፖራው አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችና የተጎዱ አካባቢዎችን ሊጎበኝ ነው

131

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችና የተጎዱ አካባቢዎችን ከታህሳስ 25 ቀን እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጎበኝ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ናቸው።

መንግስት ለዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም የሚቆይ የተለያዩ መርሃ ግብሮችን አዘጋጅቷል።

በዚሁ መሰረት ዳያስፖራው አሸባሪው ሕወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖችና የተጎዱ አካበቢዎችን ከታህሳስ 25 ቀን እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚጎበኝ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በሁለቱ ክልሎች የሽብር ቡድኑ ውድመትና ዝርፊያ የፈጸመባቸውን የተለያዩ ተቋማት እንደሚመለከቱ ገልጿል።

ከጉብኝቱ በተጨማሪ ዳያስፖራው በመልሶ ማቋቋምና በድህረ ግጭት የሚኖረውን ሚና አስመልክቶ የተዘጋጀ የጋራ የምክክር መድረክ እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

የዳያስፖራው የጉብኝት መርሃ ግብር የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ከአማራና አፋር ክልሎች ጋር በመተባባር ያዘጋጁት ነው።

የስጦታ መርሃ ግብር፣ የኪነ ጥበብ፣ የዳያስፖራ ፎረም፣ የስፖርት ክዋኔዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ገናን በላልይበላ ጥምቀትን በጎንደር፣የኢንቨስትመንት ፎረምና ዳያስፖራ እንደ ወላጅ ለዳያስፖራው ከተዘጋጁት መርሃ ግብሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የ’አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አገር ቤት ጉዞ ጥሪ’ ተቀብለው ለመጡ ዳያስፖራዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ከትናንት በስቲያ በወዳጅነት አደባባይ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

በመርሃ ግብሩ አማካኝነት ዳያስፖራው የተለያዩ መረጃዎችንና አገልግሎቶችን የሚያገኝበት ማዕከል ወደ ስራ የገባ ሲሆን፤ የ’ኢትዮጵያን ይግዙ’ በሚል መሪ ሀሳብ ለዳያስፖራው የተዘጋጁ አውደ ርዕዮችና ባዛሮችም ለጉብኝት ክፍት ሆነዋል።

መንግስት ዳያስፖራው በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም