ኢትዮጵያን የቀጣናው የሎጂስቲክስ ማዕከል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን ለመተግበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ይሰራል

ታህሳስ 21/2014/ኢዜአ/ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን የቀጣናው የሎጅስቲክስ ማዕከል ለማድረግና ዘርፉን በዓለምና በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ አማራጮችን ለመተግበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ገለፀ።

ኢትዮጵያ አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ በማዘጋጀት የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት አስቻይ ስራዎችን እየከወነች እንደምትገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር በለጠ ሞላ ገልጸዋል።

የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳለጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ወሳኝ ስርዓት መሆኑን ገልፀው፤ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን በአገሪቷ በተሟላ መልኩ ለመተግበር ቀልጣፋና ዘመናዊ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት የሆነውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርጉትን የቴክኖሎጂ አማራጮች ለመተግበር በዘርፉ ከተሰማሩ ተዋንያን ጋር በትብብር ይሰራልም ብለዋል።     

ዛሬ ይፋ የሆነው የተቀናጀ የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ስርዓት መንግስት በትራንስፖርት ዘርፍ ለተሰማሩ ተገልጋዮች የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣንና ወጪ ቆጣቢ ማድረግ እንደሚያስችለውም ተናግረዋል።   

ይህም ለኢኮኖሚ እድገት እና ለኤሌክትሮኒክስ ግብይት ማደግና መስፋፋት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው የአገሪቷ የወጪና ገቢ ጭነቶች ከ90 በመቶ በላይ በተሽከርካሪ የሚጓጓዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የተለያዩ አገልግሎቶችን አየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው ተገልጋዮች አስፈላጊ መረጃዎችን በወረቀት በመያዝ በየጊዜው በአካል መምጣት ይጠበቅባቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ አሰራር ጊዜና ወጪ ከመጠየቁ ባሻገር ለብልሹ አሰራር በር የሚከፍት፣ ዘርፉም የተደራጀ የመረጃ እጥረትና ጥራት እንዲሁም የአሰራር ስርዓት ችግር የሚስተዋልበት እንደሆነም ገልፀዋል።  

በመሆኑም ዛሬ ይፋ የሆነው የተቀናጀ  የጭነት ትራንስፖርት ማስተዳደሪያ ስርዓት በዘርፉ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታትም ያግዛል ብለዋል።

ስርዓቱ ደንበኞችን በአካል መገኘት ሳይጠበቅባቸው የትራንስፖት ብቃት ማረጋገጫ ማውጣት፣ ዓመታዊ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ማደስ፣ የተሽከርካሪዎችን ዝውውርና ተያያዥ አገልግሎቶች በበይነ መረብ እንዲያገኙ ያስችላል ነው ያሉት።  

የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎችና ረዳቶችን መታወቂያ ማውጣት፣ ማደስና ምትክ መታወቂያ መስጠትም የሚያስችል እንደሆነ ገልፀዋል።

የአገልግሎት ክፍያን በቴሌብር መፈፀም እንደሚቻል ጠቅሰው በቀጣይ በኢትስዊች አማካኝነት በሁሉም ባንኮች ክፍያ መፈፀም እንዲቻል ይሰራል ብለዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ኦፕሬተሮች በበኩላቸው ስርዓቱ ጊዜና ወጪን የሚቆጥብ፣ እንግልትና የተንዛዛ አሰራርንም የሚያሳጥር እንደሚሆን እምነት ጥለዋል።

ደንበኞች አገልግሎቱን ከነገ ጀምሮ በwww.itms.motr.gov.et ድረገጽ ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም