ለዳያስፖራዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ ይዘት ያላቸው መርሐ ግብራት ይከወናሉ

51

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 21/2014(ኢዜአ) ወደ አገር ቤት እየገቡ ለሚገኙ የዳያስፖራ አባላት ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ ይዘት ያላቸው መርሐ ግብራት ይከወናሉ ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በግሏ ለኢትዮጵያ ጥብቅና በመቆም ስትታገል የቆየችው ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ከሰሞኑ ወደ አገር ቤት እንደምትገባም ገልጿል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ሣምንታዊ መግለጫቸው የሚኒስቴሩ የ100 ቀናት ስራ አፈፃፀም ግምገማ መካሄዱን፤ በዚህም ተቋማዊ የመዋቅር ለውጡ በስኬት መጠናቀቁን ገልፀዋል።

ባለፉት 3 ወራት ዳያስፖራውን በማንቀሳቀስና ጫናውን በማርገብ ረገድ ፍሬያማው ስራዎች እንደተከናወኑም ጠቁመዋል።

ለዳያስፖራው ትናንት የአቀባበል መርሃ ግብር መከወኑንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአሸባሪው የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

ወደ አገር ቤት እየገቡ ላለው ዳያስፖራ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው በርካታ አገራዊ መርሐ ግብሮች መዘጋጀታቸውን፤ በጦርነት የተጎዱ ስፍራዎችንም እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።

ከተያዙ መርሐ ግብራት የስጦታ መርሐ ግብር፣ የኪነ ጥበብ፣ የዳያስፖራ ፎረም፣ የስፖርት ክዋኔዎች፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ ገናን በላልይበላ፣ የሚሊዮኖች ጉዞና ደም ልገሳ፣ የዳያስፖራ የድሕረ ግጭት ሚና፣ የኢንቨስትመንት ፎረም፣ ዳያስፖራ እንደ ወላጅና የምስጋና ፕሮግራም፣ ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ጠንካራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመመስረት ረገድም በኢትዮጵያ በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስ የትምህርት ክፍሎች እየተከፈቱ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ኃይል በደቡብ ሱዳን እየተወጣ ላለው ተልዕኮ በተመድ ዓለም አቀፍ አድናቆት እንደተቸረውም አንስተዋል።

ትናንት የፀደቀው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በአዋጅ መቋቋም የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ያለመ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ለኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆን የታገለችው ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ በተለይም በአሸባሪው ቡድን የሚሰነዘሩና በርካታ ግላዊ ጫናዎችን በመቋቋም ሰሞኑን ወደ አገር ቤት እንደምትገባም አምባሳደር ዲና ገልጸዋል።

ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ሚሊዮኖች ቆይታቸው በፀጥታም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች የተሳካ እንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልፀው፤ ዳያስፖራው ያለምንም ማቅማማት ወደ አገር ቤት እንዲመጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም