ቀጥታ፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት አበርክቶው ከፍ ብሏል

ሶማሊያ ነሀሴ 21/2010 በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ድጋፍ ሶማሊያ የተሻለ የፖለቲካና የምጣኔ ኃብት ቁመና ላይ እንደምትገኝ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሃሰን አሊ ካይሬ ትላንት በሞቃዲሾ በሰጡት መግለጫ፤ በአሚሶም ሥር የተሰማራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለዚሁ ስኬት ተጠቃሽ መሆኑንም ጠቁመዋል። በርካታ ሠዎች ሶማሊያ ተስፋ የቆረጠች አገር አድርገው ይመስሏታል፤ ይሁንና አገሪቱ አሚሶም በከፈለው መስዋዕትነት አሁን ላይ ተሻሽላለች ብለዋል። በዚህም የተነሳ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ፖለቲካ እንደተረጋጋ፣ ምጣኔ ኃብቷም ዳግም እንደተንሰራራና በማኅበራዊም መስክ  አዎንታዊ መሻሻሎች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት። ይህም አገሪቱ በሽብርተኝነትና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት ከማድረግ ወጥታ አሁን ላይ አገር መገንባት በሚለው ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረጓንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። በተለይም አጠቃላይ ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ሊያፋጥኑ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማጠንጠናቸውን በመግለጽ። ያም ብቻ ሳይሆን ሶማሊያ ዳግም ወደ ዓለም አቀፍ መድረኩ  እና ወደ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዳግም መቀላቀልን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ማተኮሯን ተናግረዋል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ለቀጠናው እድገት በአዎንታዊ መልኩ ድጋፍ ማድረግ የምትችልበት ሁኔታ አለ፤ ለዚህም ደግሞ የአገሪቱ ምጣኔ ኃብታዊ እድገትን ለአብነት ጠቅሰዋል። የአገሪቱ አጠቃላይ አገራዊ ምርት እድገት እንዳሳየ፣ የዋጋ ግሽበት ምጣኔም እንደቀነሰና  ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ሲገኝ  አገሪቱ የበለጠ ለአካባቢው አስተዋጽኦ እንደምታበረክት ተናግረዋል። በኢትዮጵያም ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ለቀጠናውም ሆኖ ለአፍሪካ አዲስ ተስፋ ይዞ መምጣቱን ገልጸው ይህም በአርአያነት የሚጠቀስ ሥራ መሆኑን አንስተዋል። በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን አጋርነት በተለይም ሁለቱም አገራት በመሪዎች ደረጃ የደረሱበትን መግባባትና የአገራቱን ግንኙነቱ ያድሳል ብለውታል። ጎን ለጎንም በሃያ በሰላሳ ዓመት ጊዜ ውስጥ የአገሪቱን ፖለቲካዊና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳዮች በሂደት በማስተካከል ሶማሊያ በቀጠናው ያላትን ሚና ከፍ የማድረግ ትልም አለኝ ብለዋል። በተለይም ብሔራዊ ባንክን በማጠናከር ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ጋር ቅንጅት እንዲኖረው እንዲሁም ጅምር የታየበትን የእዳ ቅነሳ ሥራ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግባራት መሆኑን አስረድተዋል። የሽብር ቡድንን ሊከላከል የሚችል ጠንካራ የጦር ሠራዊት መገንባትና በተያያዥም የመልካም አስተዳደርና የፍትህ ሥርዓት ማጠናከር ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት። ይህንንም ተከትሎ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በሶማሊያ ለማካሄድ ግብ አድርገው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ውድቀት በኋላ አለመረጋጋት የሚታይባት ሶማሊያ ባለፉት አስርተ ዓመታት አሚሶም በሰራው የሰላም ማስከበር ሥራ አንጻራዊ ሠላም እየታየባት ነው። አሚሶም ከሁለት ዓመት በኋላ በሂደት ጦሩን ከሶማሊያ ለማስወጣት እቅድ ይዟል።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም