በአሜሪካ የሚኖሩት ወይዘሮ ራሄል ደሳለኝ በአሸባሪው ህወሃት ለተጎዱ ወገኖች ያሰባሰቡት 11 ሺህ ዶላር አስረከቡ

115

ባህርዳር ፤ታህሳስ 20/2014 (ኢዜአ) በአሜሪካ የሚኖሩት ወይዘሮ ራሄል ደሳለኝ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲውል ያሰባሰቡትን 11 ሺህ ዶላር ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አስረከቡ።

በጎ አድራጊዋ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት፤ አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎችን ወረራ  በመፈጸም ያደረሰውን  ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሀገር ቤት ጥሪ ተቀብለው  ለመምጣት ሲወስኑ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚሆን በአሜሪካ ማድክሰን ከተማ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በአንድ ሳምንት ውስጥ 11 ሺህ ዶላር ማሰባሰብ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ያሰባሰቡትን ገንዘብ  በወረራው ምክንያት ለተፈናቀሉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ማቋቋሚያ ድጋፍ እንዲውል  ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አስረክበዋል።

ወይዘሮ ራሄል "እኔም ኢንጂኔር በመሆኔ በቀጣይ ከሌሎች ጓደኞቼ ጋር በመሆን በጦርነቱ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት በሙያዬ የድርሻዬን ለመወጣት ቁርጠኛ ነኝ" ብለዋል።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው፤ የሽብር ቡድኑ የከፋ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ቢያደርስም ከችግሩ ለመውጣት በውጭና ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ርብርብ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የባህር ዳር እህት ከተማ በሆነችው ማድክሰን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያደረጉት ድጋፍ አሁን ለገጠመን ችግር ከጎናችን መሆናቸውን ለወዳጅነታችን ተጨባጭ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የዜጎች  መፈናቀል ያሳሰባቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ለመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንዲውል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

''የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ባዶ እጃችንን አንመጣም፤ ለወገን ደራሽ ወገን ነው'' በሚል በአጭር ጊዜ በማሰባሰብ ያመጡትን 11 ሺህ ዶላር በወረራው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ማቋቋሚያ እንደሚውልም አረጋግጠዋል።

የተጀመረው ድጋፍም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም  ዶክተር ድረስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም