ተቋማቱ በትምህርት ማስታወቂያዎች ዙሪያ አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ በትምህርት ማስታወቂያዎች ዙሪያ አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሰልጣን ጋር በትምህርት ማስታወቂያዎች ዙሪያ አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱ በመገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩና የተዛባ መረጃ የያዙ የትምህርት ተቋማት ማስታወቂያዎችን ለማጥራት የሚያስችል አሰራርን ለማስፈን የሚረዳ ነው ተብሏል።
የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ እንዳሉት ባለስልጣኑ ቦታን ፣ትምህርት አሰጣጥን ፣ የተማሪ ቁጥርንና ጊዜን መነሻ ያደረገ እውቅናን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
የሚሰጠው ዕውቅናም በየሶስት ዓመት የሚታደስ ሲሆን ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ እንደሚያበቃና በአዲስ መልክ እንደሚሰጥ ነው ያብራሩት።
ይሁን እንጂ ባለስልጣኑ ከሚሰጠው ዕውቅና ውጪ የትምህርት ተቋማቱ ማስታወቂያዎች ያለአግባብ ሲሰራጩ እንደሚስተዋል ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ስምምነቱ ችግሩን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።
ለሀገር የሚጠቅም ብቁ ትውልድ ለማፍራት የትምህርት ተቋማትን በተመለከተ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎች ህጋዊነት መረጋገጥ እንዳለበትም ነው ያስገነዘቡት።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሃመድ እንድሪስ በበኩላቸው፤ትምህርት ለአንድ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ እድገት ወሳኝ በመሆኑ በትምህርት ዙሪያ የሚተላለፉ ማስታወቂያዎችን የሚሰሩ አካላት ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።
እነዚህ ድርጅቶች ማስታወቂያ ከመስራታቸው በፊት ወጥ ፕሮቶኮል በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ ህጋዊነቱ የተረጋገጠ ሰነድ ሲያቀርቡ ብቻ ማስታወቂያ እንዲያሰሩ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የትምህርት ስልጠና ባለስልጣንም ለትምህርት ተቋማቱ ዕውቅና የሰጠባቸውን ዘርፎች በድርጅቱ ድረ ገጽ ላይ በማስፈር ህብረተሰቡ እንዳይታለል እንዲሰራ አቶ መሃመድ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ከ57 በላይ ከፍተኛ የመንግስት ትምህርት ተቋማትና 328 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገኛሉ፡፡
የርቀት ትምህርት መርሃ-ግብርን ጨምሮ ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ የግል የትምህርት ተቋማት በሀገሪቱ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከ18 ዓመታት በፊት የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በመባል ስራ የጀመረው ተቋም በ2014 ዓ.ም ስያሜው የትምህርት ስልጠና ባለስልጣን በሚል ተቀይሯል።