የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ
ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው ከሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ነው ያጸደቀው።
ረቂቅ አዋጁ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በውይይቶች በተገኙ ግብዓቶች መሰረት በአንቀጾች ላይ ክለሳና ማስተካከያ መደረጉ ተገልጿል።
በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይም የምክር ቤቱ አባላት የረቂቅ አዋጁን ወቅታዊነት እና አስፈላጊነት ላይ ጥያቄና አስተያየት አንስተው፤ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ዕጸገነት መንግስቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ በ13 ተቃውሞ እና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።