ቀጥታ፡

የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የዘርፉ ማሕበረሰብ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ነሐሴ 20/2010 በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መምህራንና የዘርፉ ማህበረሰብ የበኩላቸውን ሚና የመጫወት ግዴታ እንዳለባቸው ተገለፀ። ይህ የተገለፀው አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 592 ተማሪዎች ዛሬ ባስመረቀበት ስነ-ስርዓት ላይ ነው። የዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ፕሬዝዳንት ዶክተር ዱቤ ጡሴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል መንግስት ከጀመረው የፖሊሲ ማሻሻያ ስራ ባለፈ መምህራንና የዘርፉ ማህበረሰብም በስነ-ምግባር የታነፀና እውቀትን የተላበሰ ዜጋ ለማፍራት ለትምህርት ጥራት መታገል ይኖርበታል። በተለይም መምህራን ቀድመው በስነ-ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ በማድረግና ለሚቀርጹት ትውልድ አርአያ በመሆን የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትሩ  ዶክተር ገመዶ ዳሌ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለአገሪቱ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማቅረብ ረገድ ባለፉት አመታት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።  በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የምትፈልገው የምስክር ወረቀት ያለው ዜጋ ሳይሆን ዕውቀትና ክሕሎትን የተላበሱ ባለሙያዎችን ነው ብለዋል። ከተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን አራት ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆነው ናትናኤል አሰፋ ሰልጣኞች ራሳቸውን አብቅተው የተሻለ እውቀት ይዘው ቢወጡ ከራሳቸው አልፎ የአገራቸውን ለውጥ ያፋጥናሉ ሲል ተናግሯል። ሌላዋ የቢዝነስ አስተዳደር የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ እመቤት ካሳሁን የትምህርት ጥራት ችግርን ለማስተካከል የሚመለከተው አካል በየደረጃው የዜግነት ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብላለች። አልፋ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ከተመሰረተ 30 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ከ77 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመርቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም