ትራንስፖርት አቅራቢዎች ለዳያስፖራው ቅንነት የተሞላበት አገልግሎት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ

ታህሳስ 19/2014/ኢዜአ/ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ዳያስፖራውን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀረበ።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ከጸጥታ ተቋማት ጋር ዳያስፖራውን ለመቀበል በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ መክሯል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዳዊት የሺጥላ የትራንስፖርት አሰጣጡን የሚያቀላጥፉ የብዙሃን፣ የአነስተኛና መካከለኛ እንዲሁም የተናጠል የትራንስፖርት አማራጮች መዘጋጀታውን ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ኢትዮጵያም ሠላም መሆኗን ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሳየት ወደ አገራቸው የሚገቡ አንድ ሚሊዮን ዳስፖራዎችን በቅንነት እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

ከውጭ የሚገቡ ቱሪስቶችን ምቾትና ተገቢውን መረጃ በመስጠት የከተማዋን ገጽታ እንዲያጎሉም ጠይቀዋል፡፡

ትራንስፖርት አቅራቢዎች በአትዮጵያዊ ጨዋነት ዳያስፖራውን በማስተናገድ አገራቸውን ይበልጥ እንዲናፍቁና ኢንቨስት የሚያደርጉበትን አማራጭ እንዲያስቡ መስራት አለባችሁም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በወንጀል የሚሳተፉ አሽከርካሪዎችም ሆኑ ባለንብረቶችን የአሽከርካሪ ፈቃድ ከመሰረዝ እስከ ሰሌዳ መንጠቅ የሚደርስ ቅጣት እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

ዳያስፖራዎቹን ለመቀበል የተጀመረው ቅንጅታዊ ዝግጅት ከአንድ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነአ ያደታ ናቸው፡፡

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ ለማክሸፍ ያደረገው ርብርብ የሚደነቅና ኢትዮጵያዊያን በማንኛውም መንገድ የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመመከት ያላቸውን አቅም ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ዳያስፖራዎቹ ወደ አገር ቤት የሚገቡት ለጉብኝት ብቻ አይደለም ያሉት ኃላፊው አንዳንድ የአውሮፓ መንግስታት የኢትዮጵያ ጸጥታ አስጊ ነው በሚል ዜጎቻቸውን እንዲወጡ በሚወተውቱበት ሠዓት አገሪቷ ሠላም መሆኗን ለማረጋገጥም ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ጌቱ አረጋ በበኩላቸው የሽብር ሀይሉ አገር ለማፍረስ የሰነዘረው ጥቃት በመከላከያና በሕዝብ የጋራ ትግል ቢከሽፍም በተስፋ መቁረጥ የጥፋት ድርጊት እንዳይፈጸም ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከዳያስፖራው ጋር ተመሳስለው የሚገቡ የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎችን ድርጊት ለመቆጣጠርም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች መታወቂያቸውን በማጣራት እንዲያገለግሉም አሳስበዋል፡፡

"የከተማዋ ጸጥታ አስተማማኝ ነው" ያሉት ኮሚሽነሩ ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ኅብረተሰቡና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው  አጠራጣሪ ጉዳዮችን ለፖሊስ እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

እንግዶችን የሚቀበሉ ሆቴሎችና አሽከርካዎች በደንበኞች ላይ የሚፈጸምን ወንጀል አለማጋለጥ በሕግ እንደሚያስጠይቅ ሊያውቁ እንደሚገባም አክለዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በበኩላቸው ወደ አገር ቤት ለሚገቡ ዳያስፖራዎች የትራንስፖርት ታሪፍ ከመቀነስ እስከ ነጻ አገልግሎት ለመስጠት በየማኅበራቸው መወሰናቸውን አሳውቀዋል።

እንግዶችን ለመቀበል ከጸጥታ አካላት ጋር የሚያገናኝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርና ወጥ የሆነ ጊዜያዊ የትራንስፖርት ታሪፍ  መመሪያ እንዲዘጋጅም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም