በእምነትና በፅናት በመቆማችን የተነሱብንን ጠላቶች በመመከት ማሳፈር ችለናል

183

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) በእምነትና በፅናት ቆመን በመታገላችን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ተባብረው የተነሱብንን ጠላቶች በመመከት ማሳፈር ችለናል ሲሉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ተናገሩ ፡፡

ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል የንግስ በዓል ዛሬ  በሀዋሳ  ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም ተከብሯል።

ከንቲባው በወቅቱ እንዳሉት፤ ለበዓለ ንግሱ ታዳሚዎች ከተማዋን የሚመጥን አቀባበልና መስተንግዶ ከማድረግ ባለፈ በቆይታቸው ሠላምና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ሐይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት የቱሪዝሙን ኢንዱስትሪ ከማነቃቃት ባለፈ የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ህብረ ብሔራዊነት በድምቀት የሚገለፅባቸው በመሆኑ ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚያሻቸውም ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ይህንን ደማቅ በዓል ስናከብር በደንብ ማስተዋል ያለብን ሀገራችንና ህዝባችንን ከውስጥም ከውጭም ተባባረው ለማፍረስ የተጠመዱ አካላት እንዳሉ ነው ያሉት ከንቲባው ይህም ሆኖ ሀገርን ለማተራመስና ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ተባብረው የተነሱብንን ጠላቶች በፅናት መክተን  አሳፍረን በመመለስ ኢትዮጵያ እንደማትፈርስ በተግባር ማሳየት ችለናል ብለዋል፡፡

በዚህ ወቅት ያሳየነውን ፅናትና አንድነት አጠናክረን በማስቀጠልም በአሸባሪው ጥቃት  የተጎዱትን ዜጎች በመርዳትና የፈረሰውን መልሶ በመስራት ሠላሟ የተረጋገጠና የበለፀገች ኢትዮጵያን መገንባት ይጠበቅብናል ነው ያሉት ከንቲባው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት እንዲሁም የጌዴኦ፣ አማሮና፣ ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ፤ እግዚአብሔር አምላካችን ለአዕምሯችን የሚከብዱ ነገሮችን ሁሉ አሳልፎልን ዛሬ በሠላም ተሰብስበን በዓል ማክበር እንድንችል አድርጎናል ብለዋል፡፡

ዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል ክብረ-በዓሉ የደመቀና ሀይማኖታዊ አስተምህሮቱን የጠበቀ እንዲሆን በቤተክርስቲያን በኩል ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ሲረባረቡ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ የበዓሉ ታዳሚ እንግዶች ሠላማቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ርብርብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ለማክበር ከሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች ከመጡ ምዕመናን መካከል የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪው  አቶ በቀለ ካሳ በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ ከዚህ በፊት ከነበረውም በላይ የክብረ በዓሉ  ድምቀት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሀዋሳ ከተማን ተዟዙረው መጎብኘታቸውንና  የፀጥታዋ ሁኔታም አስተማማኝ ሆኖ እንዳገኙትም ገልጸዋል።

ሁላችንም አካባቢያችንን በመጠበቃችንና አንድነታችንን በማጠናከራችን ከተሞቻችን ሠላም የሰፈነባቸው ሆነው ቀጥለዋል ያሉት አቶ በቀለ፤ ይህ ትብብር እስከመጨረሻው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም መጠናቀቁንና እንግዶች በከተማዋ ያላቸው ቆይታ እስኪጠናቀቅ ድረስም የተጠናከረ ፀጥታን የማስከበርና የቁጥጥር ሥራ ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየተሰራ እንደሚቀጥል የገለጹት ደግሞ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደረሰ ቡሳሮ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም