ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን ጨምሮ ከአፍሪካ ሰፋፊ የገበያ ዕድሎች ተጠቃሚ መሆን ትችላለች

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ የጎረቤት አገራትን ጨምሮ የአፍሪካን ሰፋፊ የገበያ ዕድሎች መዳረሻዋ ብታደርግ የተሻለ ተጠቃሚ እንደምትሆን ምሁራን ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ምሁራን ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልባቸው ሰፊ የገበያ አማራጮች መኖራቸውን አመላክተዋል።

የአሜሪካ መንግስት ሰሞኑን ኢትዮጵያን ከአጎዋ የቀረጥ ነጻ ንግድ ዕድል መሰረዙን ያነሱት ምሁራኑ ክፍተቱን መሙላት የሚችሉ አማራጮችን መፈለግ ጠቃሚ መሆኑን መክረዋል።

የአፍሪካ አገራት በግብርና ምርቶች፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በአትክልት ፍራፍሬና በአልባሳት ዘርፎች ያልተነካ የገበያ መዳረሻ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል።

የግብርና ዘርፍ ተመራማሪው ዶክተር ጸደቀ አባተ፤ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ይዘት ያላቸው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በጎረቤት አገራት ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

አሜሪካ ያነሳችው የቀረጥ ነጻ ዕድል የጎላ ምጣኔ ኃብታዊ ጫና እንዳያስከትል ኢትዮጵያ በአፍሪካ አገራት ሰፊ አማራጮች እንዳሉ ማየት አለባት ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅት በዓለም የምጣኔ ሀብት እድገት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አገራት ተመሳሳይ ችግር በገጠማቸው ጊዜ የነደፏቸውን ስልቶች በማስረዳትም ቻይናን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ቻይና በ1940ዎቹ ከምዕራባዊያን ጋር ጦርነት በገጠመች ጊዜ ወታደሮቿን በወባ በሽታ ለመጨረስ የመድሃኒትና ሌሎች ማዕቀቦች ተጥሎባት የወሰደችው መፍትሄ ለኢትዮጵያ ልምድ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ቻይና አገር በቀል እውቀቷን ተጠቅማ የወባ በሽታን በራሷ አቅም መፈወስ መቻሏንና ኢትዮጵያዊያን ምሁራንም ለችግሮች መፍትሄ በመፈለግ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች አገር ማስረከብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላው የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶክተር በፈቃዱ ደግፌ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ፖለቲካዊ አንድምታ ያለው በመሆኑ በምጣኔ ሃብትና ሌሎች ዘርፎች የአፍሪካ አገራት ኅብረት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ገበያ ስትልካቸው የነበሩ አስፈላጊ ምርቶች በመሆናቸው ሌሎች አገራትም ይፈልጓቸዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም የገበያ ዕድሎቹን ወደ ሌሎች አገራት ማፈላለጉ የሚፈጠረውን ክፍተት መድፈን የሚያስችል መሆኑን አክለዋል።

አማራጮችን ከመፈለግ ባሻገር የተጀመሩ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራትም ሌላው መፍትሄ መሆኑን የእንስሳት ሀብት ተመራማሪው ዶክተር ወርቅነህ አያሌው ይገልጻሉ።

ማሻሻያው በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችልና ይህም በመሰረታዊነት የበርካታ ዜጎችን ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም