የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ የለውጥ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ የለውጥ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ
አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2010 በኢትዮጵያ እየተቀጣጠለ ያለውን ለውጥ ለመጠበቅ፣ ለማስፋትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ የለውጥ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አስታወቀ። ሱዳንን በሚያዋስነው መተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራንና ነባር የይዞታ መብትን ያላስጠበቀ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቅሶ ውሳኔው በፌዴራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበትም ጠይቋል። የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ይህንን ያስታወቀው ከነሃሴ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ያካሄደውን መደበኛ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ ነው። በተለያዩ ወቅታዊና መደበኛ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን ያሳለፈው ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው ብአዴን የፖለቲካ ፕሮግራሙንና መተዳደሪያ ደንብ የህዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ግለጽ በሆነ ተሳትፎ ለማሻሻል መዘጋጀቱን ገልጿል። ፕሮግራሙ እንዲሻሻል የሚደረገው የአማራን ህዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ባህል እና ስነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ፣ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው አዳጊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖር በማስፈለጉ መሆኑንም አመልክቷል። የአማራ ብሄርተኝነት በህብረ-ብሄራዊነትና በዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ አንድነት መርህ ላይ ተመስርቶ እንዲገነባ ብአዴን በጽናት የሚታገል መሆኑንም የሥራ አስፈፃሚው መግለጫ አወስቷል። በመግለጫው ላይ አንደተመለከተው በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የህዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነጻነት የመስራትና የመኖር መብቶች በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ ብአዴን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ ይሰራል። የፌዴራላዊ መንግስቱ አባላት የሆኑ ክልሎች አከላለል በህዝቦች እውነተኛ ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝሃነትንና ሃገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ እንዲከለል ብአዴን እንደሚታገል አረጋግጧል። የአማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በህዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱ ብአዴን በምክንያት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል የሚያካሄድ መሆኑንም ገልጿል። ብአዴን ለህገ-መንግሰታዊ መብቶች መከበር በጽናት እንደሚታገል ያመለከተው የሥራ አስፈፃሚው መግለጫ ከህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎቹ መካከል አንዳንዶቹ አገሪቱ ዛሬ ከደረሰችበት የዴሞክራሲ እድገት ደረጃ ጋር ተጣጥመው መሄድ አለባቸው የሚለውን የህዝብ አስተያየትና ጥያቄ ብአዴን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል ብሏል። “እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ራሱ ያስቀመጠውን ሥርዓት ጠብቀው እስከቀረቡ ድረስ የሚነቀፉበት ምክንያት የለምና ሕጋዊና ትክክለኛ ምላሽ አግኝተው በሃገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበለጠ እንዲጠናከር ብአዴን በቁርጠኝነት ይሰራል” ሲል መግለጫው አትቷል። በዜጎች ለይ የተፈጸመን ኃላፊነት የጎደለው ኢ-ሕገ መንግስታዊ ተግባር ያወገዘው ብአዴን በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ ገብቶ የተገኘ ማንኛውም ቡድን፣ የመንግስት ባለስልጣንና ግለሰብ የሃገሪቱ ህግ በሚፈቅደው አኳኋን ለህግ ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን የሚታገል መሆኑንም ገልጿል። ብአዴን አክሎም ሱዳንን በሚያዋስነው መተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራንና ነባር የይዞታ መብትን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላትን ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ መሰጠቱን ጠቅሶ ውሳኔው በፌዴራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት ጠይቋል። በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ በተባለው አካባቢ ለጊዜው ሰፍሮ የነበረው የሱዳን ወታደርም ይዞታ እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ የካመፑም መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ በመሆኑ የሱዳን ወታደር በፍጥነት ከክልሉ ይዞታ ለቆ እንዲወጣና የፌዴራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያሰፈጽም ጠይቋል። ብአዴን በአማራ ክልል የሚገኘው ይህ የኢትዮ-ሱዳን የድንበር ጥያቄ የነዋሪዎችንና የአርሶ አደሮቻችን ይዞታ መሰረት አድርጎ፣ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅና የሃገርን ሉዓላዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡