የበጎ አድራጎት ማኅበራቱ በወልድያና አካባቢዋ ለተጎዱ ወገኖች ከ7 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ

55

ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ)  የሰሜን ወሎ ዞን ተወላጆች እና ነጃሺ በጎ አድራጎት ማኅበር በወልድያ እና አካባቢው በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አድረጉ።


ነጃሺ በጎ አድራጎት ማኅበር እና በውጭ ሀገራት እና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የሰሜን ወሎ ዞን ተወላጆች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፋን ያስረከቡት የነጃሺ በጎ አድራጎት ማኅበር ሰብሳቢ ኡስታዝ ኢንጂነር በድሩ ሁሴን ድጋፉ ለ3ኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ምግብ ነክ በሆነው ድጋፍ የስንዴ ዱቄት፣ ዘይት እና የህጻናት ምግብ፤ በተጨማሪም በርካታ ቦንዳ አልባሳት እንደሚገኝበት ተናግረዋል።

ድጋፉ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ገልጸው ሕዝቡን መልሶ ለማቋቋም የበኩላቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

በውጭ ሀገራትና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የሰሜን ወሎ ዞን ተወላጆች አስተባባሪ አቶ ታመነ መኮንን በበኩላቸው ድጋፉን ለሕዝቡ ያላቸውን አለኝታነት ለመግለጽ ማበርከታቸውንና ቀጣይነትም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የወልድያ ከተማ የሃይማኖት አባቶች ድጋፋን ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበው ሌሎችም የእነርሱን አርዓያነት እንዲከተሉ መክረዋል።

የወልድያ ከተማ ከአሸባሪው ህወሓት ወረራ ነጻ ከወጣች በኋላ ወደ ቀደመ እንቅስቃሴዋ እየተመለሰች ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም