የከተማ አስተዳደሩ ህገ-ወጥ ወረራ በተፈጸመባቸው 671 የመሬት ይዞታዎች ላይ እርምጃ ወሰደ

174

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2014 ( ኢዜአ)  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገ-ወጥ መንገድ ወረራ በተፈጸመባቸው 671 የመሬት ይዞታዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ጀማል አልዬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በመዲናዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣውን የመሬት ወረራ ለመቀልበስ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

በዚህም የተወረሩ መሬቶችን ለመለየት በተደረገው የተቀናጀ አሰራር የተደረሰበትን የኦዲት ግኝት አብራርተዋል።

በህገ-ወጥ የመሬት ወረራው ከመንግስት የስራ ሃላፊ አንስቶ በርካታ ግለሰቦችና ደላሎች መሳተፋቸውን አቶ ጀማል ገልጸዋል።

የህዝብና የመንግስት ውስን ሀብት በሆነው መሬት ከፍተኛ ወረራ እየተካሄደ መሆኑ በኦዲት ግኝት መረጋገጡን በማንሳት በዚህም 671 የመሬት ይዞታዎች በህገ-ወጥ መንገድ መያዛቸውን አንስተዋል።

በህገ-ወጥ መንገድ የተያዘው መሬት 260 ሺህ 106 ካሬ ሜትር ሲሆን ይዞታዎቹ የባለቤትነት ካርታቸው መክኖ ወደ መንግስት ካዝና መግባታቸውንም ነው ያነሱት።

በተጨማሪም ከህዳር አንድ ጀምሮ እስከ ታህሳስ 16 በተለዩ 1 ሺህ 88 ቦታዎች ላይ ህገወጥ ግንባታዎች እየተካሄዱ የተገኙ ሲሆን የተጀመሩ ግንባታዎች እንዲቆሙና እንዲፈርሱ በማድረግ የመሬት ወረራውን መቀልበስ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በተደረገው የማጣራት ስራ መሬቱን ወደ መንግስት ካዝና ገቢ ከማድረግ ባሻገር በሂደቱ ሲሳተፉ የነበሩ አመራሮች ከሃላፊነት የማንሳትና ሌሎች ፖለቲካዊ ውሳኔዎችም እንደተላለፉባቸውም አንስተዋል።

ከአመራሩ ባሻገር የመሬት ወረራ ሲፈጸም ቴክኒካል ነገሮችን ሲያመቻቸቹ የነበሩ በክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ያሉ ባለሙያዎች ከስራ ገበታቸው መታገዳቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም በጉዳዩ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ማህደራቸው ተጣርቶ ጉዳያቸው ወደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ መመራቱን ነው የገለጹት።

ከዚህ ቀደም በነበረው የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ጉዳዮች አሰራር የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ የካርታ ህትመት በማዕከል የሚታተም የነበረ ሲሆን ስርጭቱ ደግሞ በክፍለ ከተማ ይከናወን እንደነበር የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰዋል።

ሆኖም አሰራሩ ለህገ-ወጥነት የሚጋለጥ ሆኖ በመገኘቱ በየክፍለ ከተማ ያሉ 471 ሺህ ካርታዎች መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በህገ-ወጥ መንገድ በግለሰቦች እጅ የገባ ካርታ ይኖራል የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ በኋላ በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀ አዲስ የካርታ አሰራር በአገልግሎት ላይ እንደሚያውል ጠቁመዋል።

የመሬት ወረራን ለመከላከል የማጣራትና ኦዲት የማድረግ ስራው ሲሰራ ወደ መንግስት ካዝና የሚገባው መሬት እንደተጠበቀ ሆኖ መሬቱ የአርሶ አደር ሆኖ ከተገኘ ደግሞ ለአርሶ አደሩ የመመለስ ስራም እየተሰራ ነው ብለዋል።

በመዲናዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ብዛት ተከትሎ በስፋት የሚስተዋለውን የህገ-ወጥ የመሬት ወረራ ለመቀልበስ ከተማ አስተዳደሩ አሰራሩን ወደ ዲጂታል ለመለወጥ በሂደት ላይ መሆኑም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም