የትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ- ዕውቁ ሳይንቲስት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ እንደአብነት

202

በአየለ ያረጋል (ኢዜአ)

የኢትዮጵያ ጠላቶች በየዘመናቱ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ጥረዋል፤ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ የአገራቸውን ሕልውና ለማስጠበቅ ጥረዋል ግረዋል፤ ወድቀዋል፤ ተሟግተዋል። በዲፕሎማሲው ዓለምም አክሊሉ ሀብተውለድን መሰል ልጆች ተሟግተው ድል እንዳደረጉላት ሁሉ፤ በውጭ አገራት የሚኖሩ አገር ወዳዶች በራሳቸው ለአገራቸው ዲፕሎማት ሆነው አገልግለዋል። ለአገራቸው ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ተሟግተዋል። ጠላትን አርቀው፤ ወዳጅ ለማፍራት ኳትነዋል። በተለይም በአገረ አሜሪካ ከመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ተማሪ ዶክተር መላኩ በያን ጀምሮ እስከዛሬ ሌት ተቀን ለእናት አገራቸው ኢትዮጵያ ተከራክረዋል። "ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ..." እንዲሉ ኢትዮጵያዊያን ዜግነት ቢቀይሩ ስንኳ በምዕራባዊያን የተቄመችው እናት ምድራቸው ኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ እየነሳቸው ለኢትዮጵያ ዘብ ቆመው ሁለንተናዊ ተጋድሎ አድርገዋል።  

ዛሬም በክፍላተ ዓለም የተበታተኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ለማፍረስ የተነሱ ኢትዮጵያ ጠል ሃይላትን በሚችሉት ሁሉ እየታገሉ ነው። አሜሪካን ጨምሮ አንዳንድ የምዕራብ አገራት ኢትዮጵያን ለመበታተን እየኳተኑ ባሉበት የዛሬ ጊዜ ዳያስፖራዎች ዝምታን ሳይመርጡ በየአገራቱ ጎዳናዎች በነቂስ በመሰለፍ ለአገራቸው ድምጽ ሆነዋል።

ምንም እንኳ ጥቂት ባንዳዎች ከጠላት ጎን የተሰለፉ ቢሆንም በገንዘብም፣ በዕውቀትም፣ በዲፕሎማሲም ከኢትዮጵያ ጎን ተሰልፈው ተጋድሎ እያደረጉ ያሉ እልፍ አእላፍ የኢትዮጵያ ልጆች አሉ። በተለይም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአገሪቷ ፖለቲካ ተሳትፎ ተዕጽኖ የመፍጠር አቅም ስላላቸው ብርቱ ተሳትፏቸው፤ ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ውጤት ሳያስመዘግብ አይቀርም። በአሜሪካ በሚኒሶታ ግዛት የኦስቲን ከተማ ምክር ቤት አባል የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊው ኦባላ ኦባላ በቅርቡ ክፕሬዝደንት ባይደን ጋር በተገናኘበት ወቅት፤ ስለኢትጵያ ሁኔታ አስረድቶ አስተዳደራቸው አሸባሪውን ህወሓትን መደገፍ እንደሌለበት  የሞገተበት አጋጣሚም የዚህ አካል ነው።

በታላቁ ወደ አገር ቤት ጉዞ ንቅናቄ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እየገቡ ባለበት በአሁኑ ወቅት በዲፕሎማሲው ረገድ ጥረታቸውን ያላቋረጡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ምሁራንም ይገኛሉ። ለአብነትም አሸባሪው ህወሃት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ከአገራቸው ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያ ጠሉን ቡድን በማጋለጥ የቆዩትና ዛሬም ለኢትዮጵያ ትንሳኤ በቁጭት እየታገሉ ያሉት አንጋፋው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ይጠቀሳሉ። ሳይንቲስቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመ ጥር ያደረጋቸው ከ100 ዓመት በፊት በአውሮጳና በአፍሪካ ከፍተኛ ዕልቂት ላደረሰው ‘ደስታ’ የተሰኘ የከብቶች በሽታ (Rinderpest) ክትባት ማግኘታቸው ነው።

በአውሮጳዊያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1943 በኢትዮጵያ የተወለዱት ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ፤ ከዛሬ 55 ዓመታት በፊት በካሊፎርኒያ ዳቪስ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ህክምና ትምህር ቤት ተምረው በቢሾፍቱ የእንስሳት ህክምና ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት አስተምረዋል። በድጋሚ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ዳቪስ በመመለስ የ3ኛ ዲግሪያቸውን በደቂቀ ሥነ ሕይወት መስክ በማጥናት በአውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከ1980 እስከ 2006 በተማሩበት ካሊፎርኒያ እና በዋሽንግተን ስቴት ዩኒቨርሲቲ ከረዳት እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አስተምረዋል፤ ተመራምረዋል። እ.አ.አ ከ2017 ጀምሮ ’ዲስቲንጉሽድ ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ’ ሆነዋል።

እ.አ.አ ከ1990 ጀምሮ እስካሁን ድረስ ዓለም አቀፍ የሃሩራማ አካባቢ በሽታዎች የሞሌኪዩላር ባዮሎጂ ላብራቶሪ ማዕከል መስራችና ዳይሬክተር ናቸው። በእንስሳትና በሰው ላይ ለሚከሰቱ በሽታዎች በዘረመል ምህንድስና ጥበብ ክትባት ወይም መከላከያ መድሃኒት ግኝቶች ላይ ያተኮሩት ፕሮፌሰር ጥለሁን፤ የበርካታ በሽታዎች ክትባትና መድሃኒት ግኝቶች ባለቤት ናቸው።  ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በበርካታ የምርምር ተቋማት ነጮቹ ደክመው ያላሳኩትን የደስታ በሽታ ክትባት ማግኘታቸውም አንቱ አስብሏቸዋል፤ ዓለምንም በደስታ በሽታ ከሚደርሰው እልቂት ታድገዋል።

በእንግሊዝና በጣሊያን ወታደሮች ሴራ ወደ ኢትዮጵያ በገቡ ከብቶች በተዛመተው የደስታ በሽታ እ.አ.አ ከ1888 እስከ 1892 ለአራት ዓመታት በኢትዮጵያ በደረሰው እልቂት ከፍተኛ ረሀብ ተከስቶ ነበር። የፕሮፌሰር ጥላሁን የምርምራቸው መነሻ ከወላጆቻቸው ስለ ከብት መቅሰፍት ሲሰሙ በማደጋቸው መሆኑን በተለያዩ ጊዜያት ተናግረዋል። በሰውና በእንስሳት ህክምና ዕውቀት የተካኑት አንጋፋው ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን፤ ለኤች አይ ቪ/ኤዲስ ቫይረስ ክትባት ለማግኘትም ደክመዋል። ከ124 በላይ የሚሆኑ የምርምር ግኝቶች በስመ ጥር ዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች አሳትመዋል። በአሜሪካና በቻይና በሚገኙ በርካታ ተቋማትም የአካዳሚ አባልነት ተመርጠዋል፤ በአማካሪነትም እየሰሩ ይገኛል።

በተማሩበት ብሎም ባስተማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጨምሮ በአሜሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ዕውቅናና ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ለአብነትም የዩኒቨርሲቲዎች የምርጥ አስተማሪነትና ተመራማሪነት ሽልማት፣ የእንስሳት ህክምና ዘርፍ ከፍተኛውን ዓለም አቀፍ ሽልማት፣ የልዩ አገልግሎት ሽልማቶች ተበርክተውላቸዋል።

እርሳቸው በሚመሩት የዓለም አቀፉ የሃሩራማ አካባቢ በሽታዎች የምርምር ማዕከል ከተለያዩ ታዳጊ አገራት በርካታ ሳይንቲስቶችንም አፍርተዋል። እኒህ ጉምቱ ሳይንቲስት ግን በሳይንሳዊ ምርምር ብቻ አፍሪካን በተለይም ኢትዮጵያን በማገዝ ብቻ አልተቆጠቡም። ይልቁኑም ለአገር ሕልውና ስጋት የሆነው የአሸባረውን ቡድን ክፋት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ስለተገለጠላቸው በዓለም አቀፍ እና አገር ውስጥ ሚዲያዎች በሃሳብ ታግለዋል። በእስካሁኑ የሶስት አስርት ዓመታት ትግላቸውም ወያኔ የኢትዮጵያ ካንሰር በመሆኑ መወገድ እንዳለበት፤ ኢትዮጵያም ከምዕራባዊያን ባለፈ ቻይናን መሰል አገራት ጋር ትስስሯን እንድታጠናክር ወትውተዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የሀገራቸውን ሕልውና የሚጎዱ የአንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት ጫናዎችን በተለይም የአሜሪካና እንግሊዝን የተሳሳተ አካሄድ መከላከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ለአብነትም በ1980ዎቹ መጨረሻ ገደማ ወደስልጣን የወጣው የትሕነግ ቡድን ኢትዮጵያዊያንን በዘር ከፋፈሎ አገሪቷን ለመዝረፍና ለማዳከም የተነሳ ማፊያ እና ዘረኛ ስብስብ እንደሆነ በተከታታይ በርካታ አርቲክሎችን ጽፈው ነበር።

ዕውቁ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ጥላሁን ይልማ ከሰሞኑም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የያዘችውን አቋም የሚኮንን ቅሬታ ለካሊፎርኒያ ግዛት ተወካይ ኮንግረስ አባል ለሆኑት ጆን ጋራመንዲ/John Garamendi/ ደብዳቤ ፅፈዋል። በደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያን በዘርና በጎሳ ከፋፍሎ ለማጥፋት ሲሰራ የነበረውን አሸባሪውን የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርን በማደራጀት እና በገንዘብ በመደገፍ አሜሪካ ሚና አላት በሚል ኢትዮጵያዊያን ቅሬታ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። በዚህም በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1972 የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ሄንሪ ኪሲንገር የወደፊቷን ኢትዮጵያን በተመለከተ ያቀረቡት ሚስጥራዊ መረጃም አንስተዋል። በበርካታ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የደህንነት አማካሪነት እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት የአሜሪካዊ ፖለቲከኛ ኪሲንገር ያሳሰቡበት መረጃም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኢትዮጵያን በሃይማኖት፣ በዘውግ፣ ወይም በሌላ የመከፋፈያ አጋጣሚዎች ሁሉ ከፋፍሎ በማያባራ ግጭት ማጥ ውስጥ በመክተት አገሪቷን ማዳከም ላይ አበክራ መስራት እንዳለባት የሚመክር መሆኑን ገልጸዋል።

በቅርቡ እንኳ ቻይና እና ሩስያ ከጎኗ ባይቆሙ ኖሮ አሜሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ያላትን አድራጊ ፈጣሪነት በመጠቀም ተጨባጭነት በሌለውና በሀሰት በተደራጀ መረጃ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ዘር ጭፍጨፋ አደርጓል የሚል ሰነድ አዘጋጅታ እንዲጸድቅ መጣሯን ጠቅሰዋል። ይህ አስደንጋጭ ጭካኔና ኩናኔ የአሜሪካ መንግስት የማን አለብኝነት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል። ቀደም ባሉ ዓመታትም በጄሚ ካርተር፣ በቢል ክሊንተን፣ በባራክ ኦባማና መሰል የዲሞክራት ፕሬዘዳንቶች ዘመን ሳይቀር ኢትዮጵያ ለመልከ ብዙ ተግዳሮት እንድትዳረግ መደረጓን ገልጸው፤ አሁንም በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ይህ ተደግሟል ነው ያሉት።

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው እና ከልክ ያለፈው ጉዳይ ደግሞ በአፍሪካ ቀዳሚ በሆነው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የተሰነዘረው የስም ማጥፋት ዘመቻ ነው ብለዋል። አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እና ሲ.ኤን.ኤን መሰል የምዕራብ ሚዲያዎች አሸባሪው ቡድን አዲስ አበባን ሊቆጣጠር እንደሆነ በመግለጽ ዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ለቆ እንዲወጣ ሲያደርጉት የነበረውን ቅሰቀሳም ክፉኛ ኮንነዋል። ይህ ሀሰተኛ ቅስቀሳም በተለይም የአፍሪካ ህብረት ሰራተኞች አዲስ አበባን እንዲለቁ ያለመ የሽብር መንዛት ድርጊት ነው ብለዋል። በዚህም በኮንግረሱ ስለኢትዮጵያ የማያወላውል አቋማቸውን ይዘው እንዲሞግቱ ፕሮፌሰር ኤሜሪተስ ጥላሁን ጠይቀዋል።

ፕሮፌሰር ጥላሁን ከዚህ ቀደም ብሎም ለተለያዩ የአሜሪካ መንግስታት ባለስልጣናት ደብዳቤ ጽፈዋል። ለአብነትም ከሳምንታት በፊት ለአሜሪካ ህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ እና በኦክላሆማ ለሪፐብሊካን ተወካይ ሴናተር ጂም ኢንሆፍ በህዝብ በተመረጠ ሕጋዊ የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጥቃት የከፈተን አሸባሪ ቡድን የባይደን አስተዳድር እያደረገለት ያለውን ድጋፍ ተቃውመው ደብዳቤ ጽፈውላቸው ነበር። በደብዳቤያቸውም አሜሪካዊ ዜግነት እንዳለው ሰው የትኛውንም ምርጫ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንደነበራቸው፤ ይባስ ብሎም የዲሞክራቶች ደጋፊ ሆነው በገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አትተዋል። ከእንግዲህ ወዲያ ግን የባይደን አስተዳደር ሽብርተኛውን ቡድን መደገፍ እስካላቆመ ድረስ በየትኛውም የአሜሪካ ምርጫዎች (በፕሬዝዳንት፣ በህግ መወሰኛ እና በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ምርጫዎች) ዲሞክራቶችን ደግፈው እንደማይሰለፉ ይልቁኑም ዲሞክራቶች በአገሪቷ ምክር ቤቶች በአባላት ብዛት ብልጫ እንዳይኖራቸው በተቃራኒ እንደሚሰሩ አሳስበዋል።

ባለፈው ዓመት ወርሃ ሚያዝያ የኦክላሆማ ግዛት ሴናተር ጂም ኢንሆፍ ዋሽንግተን በኢትዮጵያ የስራ ሃላፊዎች ላይ የጣለችውን የቪዛ ክልከላ በመቃወም፤ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት እና እርምጃው ሰላማዊ ውሳኔዎች ላይ ለመድረስ እንደማይጠቅም አሳስበነው ነበር። በተመሳሳይ የካሊፎርኒያው ኮንግረስማን ጆን ጋራመንዲ(ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በፊት ከባለቤታቸው ጋር በኢትዮጵያ የሰላም ጓድ የነበሩ) ከሁለት ዓመታት በፊት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ድርድር አሜሪካ ከግብጽ ወግና በምትንቀሳቀስበት ወቅት ለአገሪቷ ገንዘብ ሚኒስትር በፃፉት ደብዳቤ አሜሪካ በግድቡ ድርድር ዙሪያ ራሷን ገለልተኛ ሚዛናዊ ማድረግ እንዳለባት፤ የፖለቲካ መፍትሔ ለመስጠት ማስገደድም ይሁን ጫና መፍጠር በፍጹም አዋጪ እንዳይደለ ገልጸው ነበር። ስለሆንም እንዲህ አይነት የኢትዮጵያ ወዳጅ ሴናተሮች እና ኮንግረስማኖች እውነቱን በማስገንዘብ ረገድ ፕሮፌሰር ጥላሁንን መሰል ተውልደ ኢትዮጵያዊያን ጉልህ ሚና እንደነበራቸው መገመት ይቻላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም