ለጸጥታ ሃይሉ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን

44

ደብረ ማርቆስ ፤ ታህሳስ 18/2014 (ኢዜአ) የሀገር ሕልውናን ለመጠበቅና ሰላምን ለማረጋገጥ በግንባር ለተሰለፈው የጸጥታ ሃይል የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የደብረ ማርቆስ ከተማና አካባቢው  ነዋሪዎች 32 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዓይነት ድጋፍ  በማሰባሰብ ለህልውና ዘመቻው ማበርከታቸው ተመልክቷል።

የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር ያለው፤ ለእናትና ለህጻናት የማይራራ የአሸባሪው ህወሃት ወራሪ ቡድንን ለመመከት ለተሰለፈው የፀጥታ ሃይል አንድነታቸውን አጠናክረው የደጀንነት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ለኢዜአ ተናግረዋል።

የአሸባሪውን ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራውን በማክሸፍ የህልውና ደጀን ለሆኑት የፀጥታ ሃይሎች በጉልበታቸው፣ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ በማዋጣት የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑን ጠቅሰው ፤በግላቸው 5 ሺህ ብር  የሚገመት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን 2 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ  እና 50 ኪሎ ግራም የምግብ እህል ድጋፍ  ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ነጋሽ ዋሌ በበኩላቸው ለሀገርና ለህዝብ መከታ ለሆነው የፀጥታ ሃይል  ድጋፋቸውን  አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የከተማው የስንቅ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ይልቃል ሽበሽ እንዳሉት፤ ካለፈው የጥቅምት ወር ወዲህ ህብረተሰቡን በማስተባበር 32 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና ከ14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት  የዓይነት ድጋፍ  በማሰባሰብ ለህልውና ዘመቻው ተበርክቷል።

የከተማውና አካባቢው ማህበረሰብ በግንባር ላለው የፀጥታ ሃይል በደጀንነት የሚያደርገውን ድጋፍ  መቀጠሉንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም