ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ጉባኤ በመጪው ሳምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2010 የምስራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስድስተኛ ዓመታዊ ጉባኤ በመጪው ሳምንት መጨረሻ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። ከነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም  ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተዘጋጀው ጉባኤ "ትኩረት ለቀጠናው ንግድ፣ ኢነርጂና የግልግል ዳኝነት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው። የግልግል ዳኝነት ተከራካሪ ወገኖች ጉዳያቸውን የሚያይላቸው ሶስተኛ ገለልተኛ አካል በመሾም የሚከናወን የግጭት ወይም አለመግባባት አፈታት ዘዴ ነው። የአፍሪካ አገራት በንግድ፣ በመሰረተ ልማትና በኢነርጂ የሚያስተሳስሯቸውን ስምምነቶች በመፈረም ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ነጻ ንግድን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት መካከል በንግድና ኢንቨስትመንት መስኮች የተፈረሙ ስምምነቶች በሚተገበሩበት ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን መፍታት የሚቻልበትን ስልት መዘየድ የውይይት መድረኩ ዋነኛ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደሚሆን የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል። ከዚህም ሌላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የግልግል ዳኝነት ስርዓት ተሞክሮዎችን ከአፍሪካ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለመጠቀምና የግልግል ዳኝነት ተቋማትን አቅም ለማጎልበት የሚያግዘ መላ መዘየድም የውይይት መድረኩ አጀንዳ መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል። በጉባኤው ላይ የግልግል ዳኝነት ባለሙያዎች፣ የፍርድ ቤት ዳኞች ጠበቆችና አቃቤ ህጎች፣ ዓለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ተቋማት፣ የመንግስት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። ከጉባኤው መሪ ቃል ጋር የተያያዙ የመነሻ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደርግባቸውም ታውቋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በጉባኤው ላይ ንግግር ከሚያደርጉና የመነሻ ጽሁፋቸውን ከሚያቀርቡት መካከል ናቸው ተብሏል። ጉባኤው የተለያዩ የግልግል ዳኝነት ባለሙያዎችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ በመሆኑ በዘርፉ ጠቃሚ ልምድ ለመለዋወጥ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል ነው የተባለው። ኢትዮጵያ ጉባኤውን ስታስተናግድ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ባለፈው ዓመት በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ የተካሄደው አምስተኛው የምስራቅ አፍሪካ ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ጉባኤ "ዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት ስርዓትና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ያላቸው ትስስር" የሚል መሪ ሀሳብ  ነበረው። ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ ሌሎች ጉባኤውን ያስተናገዱ አገራት ናቸው። የግልግል ዳኝነት በባህሪው ከፍርድ ቤት ክርክር ሂደትና ከሌሎች አማራጭ የሙግት መፍቻ ዘዴዎች ጋር የሚያመሳስለው በዳኞቹ የተወሰነው ውሳኔ አስገዳጅና በፍርድ ቤቶች ተፈጻሚነት ያለው በመሆኑ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በግልግል ዳኝነት ለጉዳዩ ውሳኔ ለመስጠት የሚፈጀው ጊዜ በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ከሚወስደው ጊዜ በጣም ያነሰ ነው ይባላል። ይህ ደግሞ ተከራካሪዎች በክርክር ሂደት የሚያጠፉትን ጊዜ እና ገንዘብ ስለሚቀንስ ጠቃሜታው የጎላ እንደሆነ ይነገራል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም