በድሬዳዋ አስተዳደር ለ17 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሰራ ነው

38

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ)በድሬዳዋ አስተዳደር በተያዘው ዓመት ለ17 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የአስተዳደሩ የሥራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ገለጹ።

ባለፉት አምስት  ወራት 4 ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች ሥራ እድል ተፈጥሯል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ሮቤል ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የተበታተኑ ተግባራትን በአንድነት አጣምሮ የተመሠረተው ቢሮ  ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

ይህም በየቦታው የተበታተኑ ተግባራት በአንድ ስፍራ በመሰባሰባቸው ዘንድሮ ለ17 ሺህ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የተያዘውን ውጥን ለማሳካት መደላደል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት በቀድሞ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በአዲሱ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የድሬዳዋ ጣቢያና በመንግሥት ተቋማት ሥራ መፈጠሩን አቶ ሮቤል ተናግረዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ገበያና ፍላጎት ተኮር ሥልጠና በመስጠትና የተማሩትን ወጣቶች በኢንተርፕራይዞች በማደራጀት  የስልጠና፣ የብድርና የገበያ ትስስር እየተፈጠረላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቢሮው የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለሙያ አቶ ደመላሽ እሸቱ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ወራት 3ሺህ 300  ለሚሆኑ ሰዎች በቋሚነትና  ከ600 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ጊዜያዊ ሥራ መፈጠሩን  ተናግረዋል፡፡

በግብርና፣ በአገልግሎትና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ሰዎች መካከል ገሚሶቹ ሴቶች መሆናቸውን  አስረድተዋል፡፡

ሥራ ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት ራጂ መሐመድ ፤በድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተገነቡ ሼዶች በሙሉ ሥራ ቢጀምሩ በርካታ  ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግሯል፡፡

''እኔ በዚህ ፓርክ  ሥራ ከጀመርኩ በኋላ ከሱሴ ተገላግያለሁ፤ ህይወቴ ተለውጧል፤ ለሀገሬና ለድሬዳዋ ሰላምና ዕድገት አስተዋጽኦ እያደረግኩ መሆኑ ያኮራኛል'' ብሏል፡፡

ሌላኛው ወጣት ግርማ ገመቹ በበኩሉ፤ ወጣቶች ሥራ መጠበቅ ሣይሆን በተማረው ሙያ ተደራጅቶ ሥራ መፍጠር እንዳለበት አመልክቷል፡፡

በከተማው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሥራ አጥነት ምጣኔን ከ21 በመቶ ወደ 7ነጥብ 5 በመቶ ለማውረድ እንደሚሰራ ከአስተዳደሩ የሥራ ክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ገለጻ መረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም