ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀለው ሁለተኛ ክለብ የሚለይበት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀለው ሁለተኛ ክለብ የሚለይበት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2010 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን የሚቀላቀለው ሁለተኛ ክለብ የሚለይበት የከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ነገ ይካሄዳሉ። ባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በሁለት ምድብ ተከፍሎ እየተካሄደ በሚገኘው የ2010 ዓ.ም ከፍተኛ ሊግ በምድብ ሀ ባህርዳር ከተማ አንደኛ ሆኖ በማጠናቀቅ በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መሳተፉን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው። በሁለቱም ምድቦች 16 ክለቦች ይገኛሉ። ከፍተኛ ፉክክር እየተካሄደበት በሚገኘው ምድብ ሁለት የሚደረጉ የመጨረሻ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባህርዳር ከተማን ተከትሎ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚመጣውን ክለብ ያሳውቃል። ነገ በተመሳሳይ ከረፋዱ 4 ሰዓት በሃዋሳ ስታዲየም ደቡብ ፖሊስ ከድሬዳዋ ፖሊስ፣ ሆሳዕና ላይ ሀዲያ ሆሳዕና ከጅማ አባ ቡና ፣በደቡብ ኮሌጅ ሜዳ ወልቂጤ ከተማ ከሀላባ ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው። ደቡብ ፖሊስ በምድብ ሁለት በ58 ነጥብ ምድቡን እየመራ ሲሆን ጅማ አባ ቡናና ሀላባ ከተማ በተመሳሳይ 56 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል። ደቡብ ፖሊስ ድሬዳዋ ፖሊስን ካሸነፈ ወደ ፕሪሚየር ሊግ መግባቱን የሚያረጋግጥ ሲሆን ጅማ አባ ቡናና ሀላባ ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመግባት የደቡብ ፖሊስ አቻ መውጣት ወይም መሸነፍ ይጠብቃሉ። ደቡብ ፖሊስ ከ58 ነጥብ በተጨማሪ 33 የግብ ክፍያ ያለው ሲሆን ጅማ አባ ቡና 30 እንዲሁም ሀላባ ከተማ 24 የግብ ክፍያ አላቸው። በዚሁ መሰረት ጅማ አባ ቡና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለማደግ ደቡብ ፖሊስ አቻ ወጥቶ ወይም ጅማ አባቡና ሀዲያ ሆሳዕናን ከ3 ጎል ልዩነት በላይ ማሸነፍ አለበት። ጅማ አባ ቡናና ደቡብ ፖሊስ ተሸንፈው ሀላባ ከተማ ካሸነፈ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደግ ይችላል ማለት ነው። በአጠቃላይ ሲታይ ደቡብ ፖሊስ ከሁለቱ ክለቦች አንጻር የተሻለ ዕድል አለው። ሶስት ክለቦች ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያልፉ ሲሆን በሁለቱ ምድቦች ሁለተኛ የወጡ ቡድኖች እርስ በእርስ ተጫውተው ያሸነፈው ቡድን ፕሪሚየር ሊጉን የሚቀላቀል ሶስተኛ ክለብ ይሆናል። በዚሁ መሰረት በምድብ ሀ ሽሬ እንዳስላሴ ባህርዳርን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን በምድብ ለ ሁለተኛ የሚወጣው ቡድን ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይታወቃል። ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚገባውን ሶስተኛ ቡድን ለመለየት የሚደረገው የመለያ ጨዋታ ነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን የከፍተኛ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊን የሚለየው የዋንጫ ጨዋታ ደግሞ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም እዛው ድሬዳዋ የሚካሄድ ይሆናል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኢትዮ ኤሌትሪክ፣ አርባምንጭ ከተማና ወልዲያ ከተማ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸው የሚታወስ ነው።