ለገናን በዓል ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
ለገናን በዓል ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎችን ለማስተናገድ ተዘጋጅተናል
አዳማ ፤ ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎች ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አሰታወቀ።
ቢሮው በአዳማ ከተማ ከሆቴሎችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር ያለውን ዝግጅት በተመለከተ ዛሬ መክሯል።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሳዓዳ ዑስማን እንደገለጹት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት ከሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑትን እንደ ኦሮሚያ ክልል ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጅቱ ተገባዷል።
ለዚህም አመቺ የአገልግሎትና መስተንግዶ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
እንግዶቹን በኦሮሚያ በአራቱም አቅጣጫዎች በማስጎብኘት የቱሪዝም መዳረሻዎች፣የልማትና የኢንዱስትሪ ሴክተሮችን እንዲመለከቱና በቀጣይ የራሳቸውን ድርሻ ጭምር ማበርከት እንዲችሉ እየሰራን ነው ብለዋል።
በዋናነት እንደ ኢትዮጵያ አንድ ሆነን እንድንቆም በውጭ ያሳዩትን አንድነት በሀገራቸው እንዲደግሙ ተስፋ አለን ያሉት ወይዘሮ ሳዓዳ ፤ በተለይ ሆቴሎች እንዴት እንግዶቻቸውን መቀበልና ማስተናገድ ብሎም ተገቢውን አገልግሎት በቅናሸ እንዲሰጡ ዝግጅት መደረጉን አረጋግጠዋል።
የተሻለና ተወዳዳሪ የሆነ አገልግሎት በመስጠት እንግዶችን ማስደሰት ከሆቴል ባለቤቶች እንደሚጠበቅ ያመለከቱት ሃላፊዋ፤ ለዚህም ሁሉም በእኩል ግንዛቤ መዘጋጀት አለበት ነው ያሉት።
የከተማ አስተዳድሮችም የፀጥታ፣ፅዳት፣የመብራትና ሌሎችንም አገልግሎቶችን ከወዲሁ አስተካክሎ በማመቻቸት እንግዶቻችን መቀበል አለብን ሲሉ ወይዘሮ ሳዓዳ አብራርተዋል።
በአዳማ ከተማ የሪፍት ቫል ሆቴል ተወካይ ወይዘሮ ጀሚላ ነገዎ በበኩላቸው ወደ ሆቴላቸው ለሚመጡ እንግዶች የ30 በመቶ ቅናሽ በማድረግ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የመኝታ ክፍሎችን በማደስ ለእንግዶች ምቹ ማድረጋቸውን ገልጸው፤ አስተናጋጆችና የሆቴሉ ሠራተኞች የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ የኮሮና መከላከያ ፕሮቶኮልን መሰረት ባደረገ መልኩ መሰናዳታቸውን ተናግረዋል።
"ከውጭ የሚመጡ እንግዶቻችን እኛንና ሀገራችን ብለው የሚመጡ በመሆናቸው ምንም ዓይነት የዋጋ ጭማሪ ሳይኖር በቅናሽ ዋጋ የተሻለ አገልግሎት እንሰጣለን" ያሉት ደግሞ የኬኤም ኢንተርናሽናል ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ ወርቅነህ ናቸው።
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከወዳጆች ጋር በመሆን ሀገርን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች የተሸረበውን ሴራ በማክሸፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን አውስተዋል።
ጠላትን በመመከት በሀገሪቱ የተመዘገበው ስኬት አስደሳች መሆኑ ጠቅሰው፤ እንግዶቹም በዓሉን ከሀዝባቸው ጋር ሆነው በደስታ እንዲያሳልፉ ተቀብለው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
"በተለይ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ለዓለም ማህበረሰብ ለማስረዳትና ከውጭ ሆነው የሐሰት አሉባልታ ለሚነዙ ጠላቶች ምላሽ ለመስጠት እንደሆነም ተገንዝበን በአግባቡ ልናስተናግዳቸው ይገባል " ብለዋል አቶ ከበደ።
ለገና በዓል አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ እንግዶቹን ለመቀበል ዝግጅት እያደረግን ነው ያሉት ደግሞ የአዳማ ራስ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ሀሳብነህ እንግዳ ናቸው።
በተለይ የሆቴሉ አስተናጋጆች ስለሚመጡት እንግዶቻችን አቀባበል ተገቢውን ግንዛቤ እንዲያገኙና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አድርገናል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ የመኝታና አገልግሎት ዘርፉን አስተካክለው በማስዋብ እንግዶችን ለመቀበል መሰናዳታቸውን ገልጸዋል።
"ዳያስፖራው ሀገራችን ላይ የተደቀነው አደጋ ለመቀልበስ ከጫፍ እስከ ጫፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሀገር ባለ ውለታ በመሆናቸው እነሱን ለማስደሰት ተዘጋጅተናል፤ አሁን ከምንሰጠው አገልግሎት ዋጋ ቀንሰን ለማስተናገድና ምቾት እንዲሰማቸው ለማድረግ እንፈልጋለን" ብለዋል።
አዳማ ከአዲስ አበባ በቅርበት ርቀት ላይ በመሆኑ በርካታ ዳያስፖራዎች ይመጣሉ ብለው እንደሚጠብቁና ለዚህም የሚመጥን መሰናዶ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።