ቀጥታ፡

ዋልያዎቹ ከብሩንዲ ጋር ነሐሴ 27 የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ ነሀሴ 20/2010 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም ከብሩንዲ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል። ቡድኑ በ2019 ካሜሩን በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ጳጉሜን 4 ቀን 2010 ዓ.ም በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከሴራሊዮን ጋር የምድብ የማጣሪያ ጨዋታ ያካሂዳል። ለዚህም ዝግጅት በኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ የሚሰለጥነው ብሔራዊ ቡድን 34 ተጫዋቾችን በመያዝ ከነሐሴ 3 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሃዋሳ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛል። በብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካኝነት በተደረገ ጥረት የብሩንዲ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆኑ ነሐሴ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በሃዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ጨዋታውን እንደሚያደርግ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። የወዳጅነት ጨዋታው ዋልያዎቹ ከሴራሊዮን ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ መጫወቱ ቡድኑ አቋሙን ለመፈተሽ የሚያስችለው እንደሆነ ታምኖበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሮን በቀጣዩ ዓመት ለሚደረገው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በምድብ አምስት ከኬንያ፣ጋናና ሴራሊዮን ጋር ተመድባለች። ዋልያዎቹ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያካሄዱት ሰኔ 2009 ዓ.ም በባባ ያራ ስታዲየም ከጋና አቻው ጋር ሲሆን በውጤቱም ብሔራዊ ቡድኑ 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት መሸነፉ የሚታወስ ነው። ጋናና ሴራሊዮን የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን በማሸነፍ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን ኬንያ ሶስተኛ ኢትዮጵያ የመጨረሻውን አራተኛ ደረጃ ይዛለች። በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም በፊፋ የአገራት ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደረጃውን ሳይቀይር በነበረበት 151ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በካሜሮን በሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ይሳተፋሉ።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም