የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ዓለም ሊገነዘብ ይገባል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ዓለም ሊገነዘብ ይገባል- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ባህርዳር፣ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ )ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከውጭ አገራት ጋር የምታካሂደው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመርህ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ዓለም ሊገነዘብ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስገነዘቡ።
"የሀሰት መረጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ያሳደረው ጫና" በሚል መሪ ሃሳብ በባህርዳር ከተማ የምክክር ጉባኤ ተካሂዷል።
አምባሳደር ዲና በጉባኤው ላይ እንደገለጹት ኢትዮጵያ እንደ አፍሪካ አንድነትና የተባበሩት መንግስታት አይነት ድርጅቶችን ከመሰረቱ አገራት አንዷ ናት።
ከጥንት ጀምሮ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች በውጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው ሶስት አላማዎች ላይ በመመስረትና በማተኮር ይንቀሳቀሱ እንደነበር ገልጸዋል።
የአገራችን ሉአላዊነትና ሃገረ መንግስትን ማስከበርና ማስጠበቅ፣ ዓለም አቀፍ ድጋፍ በማሰባሰብ የማዕከላዊ መንግስትን ማጠናከር፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ ማግኘት የሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ግንኙነቶች ተተኳሪዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።
"አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ አመራርም ከሞላ ጎደል ይህንኑ አቅጣጫ እንደሚጠቀም አመልከተዋል ።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ላይ የሚካሄደው በሃሰተኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ተጽእኖ የመፍጠር እንቅስቃሴ የኢትዮጵያን ታሪክ ካለማገናዘብ የመጣ ተጽእኖ በመሆኑ ሊታረም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በበኩላቸው የዓለም የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የሚፈበረከው በዓለም ላይ ባሉ አራት አካላት ነው።
የስለላ ድርጅቶች የሃሰት ፕሮጋንዳ ስሪት ምንጭ ሲሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች በማጮህና መገናኛ ብዙሀን ደግሞ በማስተጋባት መሪ ተዋናይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የሃያላን አገራት መሪዎች ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች ያመነጩትንና የጮሁትን ጉዳይ መረጃ አግኝተናል በማለት ማውገዝና አላማቸውን ለማሳካት ሲጠቀሙበት ማየት የተለመደ መሆኑን ጠቁመዋል።
"በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ያለው አለም አቀፍ ጫናና ውግዘትም በነዚህ አካላት ቀድሞ የተፈበረከ በመሆኑ እወነቱን ለማስረዳት ቢሞከርም ሊገነዘቡት እንደማይችሉ ተረድቶ አማራጭ መፍትሄ መፈለግ ይገባል" ብለዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጨው አብዝሃኛው የሃሰተኛ መረጃ መሆኑን በዓለም ላይ የተካሄደ ጥናትን ጠቅሰው ያረጋገጡት ደግሞ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ ናቸው።
ፌስቡክና ትዊተር የተባሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን አስመልክቶ ከሚያሰራጩት መረጃ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆነው ሃሰተኛ መረጃ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።
የሃሰተኛ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማቶችና ሌሎች ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀንና ድርጅቶች ጭምር የሚሰራጭ መሆኑን የጉባኤው ተሳታፊ ምሁራን በመገንዘብ መመከት እንደሚገባ ዶክተር ፍሬው አሳስበዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የክብር ዶክተር ኦባንግ ሚቶ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ አማላይ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ሰፊ ህዝብና የስራ ተነሳሽነት ያለው ወጣት ያላት አገር ናት" ብለዋል።
ሀገሪቱ አሁን ላይ ከውጭና ከውስጥ ያሉ ጠላቶቿ በማበር ከባድ ፈተና የደቀኑባት ቢሆንም አንድነታችን በማጠናከር ፈተናውን ማለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
"ያለንን የተፈጥሮ ጸጋና ሃብት በአግባቡ አልምተን ለመጠቀምም በአንዳንድ ምዕራባውያን የሃሰት ፕሮፓጋንዳ የተወሰደውን ማንነታችን መመለስ አለብን" ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዲፕሎማሲ ሁኔታ፣ ተግዳሮቶችና የቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚያመላክቱ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።