የአገሪቱን ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምክር ቤቱ አስገነዘበ - ኢዜአ አማርኛ
የአገሪቱን ጥቅም ለማስከበር የተጀመሩ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ምክር ቤቱ አስገነዘበ
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገሪቷን ጥቅም ለማስጠበቅ የጀመራቸውን የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራትን አጠናክሮ እንዲቀጥል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ። ምክር ቤቱ የሚኒስቴሩን የ2010 በጀት ዓመት የ9 ወራት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ አድምጧል። የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የአገሪቷን ጥቅም ለማስከበር የሚያደርገውን ሁሉን አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠል አለበት። የባለብዙና የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ከልዩ ልዩ አገሮች ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ከአለምና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመገናኘት የኢትዮጵያን ጥቅሞች ማስጠበቅ መቻሉ የሚደነቅ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። በዓባይ ወንዝ ላይ በየጊዜው የሚነሱ ተለዋዋጭ እንቅፋቶችን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመፍታት፣ ችግር እንዳይከሰት በመከላከል፣ በወንዙ ላይ በፍትሐዊነት የመጠቀም መብት እየተረጋገጠ መሄዱ የአገሪቷ የዲፕሎማሲ ጥንካሬ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚደርስባቸውን ችግርና የመብት ጥሰት በማስቆም ከ41ሺህ በላይ ዜጐች መብታቸው እንዲከበር፣ ከስደት እንዲመለሱና የሰሩበትን ገንዘብ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚሰራው ሥራ እንዲጠናከር አስገንዝበዋል። በስትራቴጂካዊ አጋርነት ፕሮግራም በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲሰፍን፣ በአገሮች መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠርና የጅቡቲ የባቡር መስመር ዝርጋታ እንዲጀምር አበረታች ተግባራት መከናወናቸው ተጠቁሟል። 'በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ጽህፈት ቤትን ለመገንባት መሬት በነፃ እንዲገኝ፣ የጅቡቲ ወደብ አገልግሎት በ23 በመቶ እንዲቀንስ፣ አስተማማኝ የወደብ አማራጭ እንዲኖር የተለያዩ ስምምነቶች ላይ እንዲደረሱ የተሰሩት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው' ሲሉ አብራርተዋል። ዳያስፖራው በአገሪቷ ልማት ላይ የበለጠ እንዲሳተፍ የሚኖርበትን አካባቢ የማወቅ፣ የመመዝገብና በልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በማሳተፍ አገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አቶ ተስፋዬ አሳስበዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየው በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሹመት የሚመደቡ አምባሳደሮች በእውቀት፣በክህሎትና በሙያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየተሰራ ነው። ኢትዮጵያ በቀጠናው የሰላም ደሴትነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተጀመረው ጥረት በአሁኑ ወቅት ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ አስረድተዋል አገሪቷ በምትከተለው የውጭ ግንኙነት ላይ ጉልህ ተጽህኖ የሚኖራቸውን ጉዳዮች በመለየት 18 ጥናቶችን ለማካሄድ ታስቦ 16ቱ ጥናቶች ተጠናቀው ለዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ግብዓት መደረጉን ጠቁመዋል። ለኤርትራ መንግስት የፀብ አጫሪነትና ትንኮሳ ተመጠጣኝ ምላሽ መንግስት የሰጠው ምላሽ እንደተጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው በአገሮቹ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል የሰላም ድርድር ለማድረግ ዝግጁነት መኖሩን አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ከግብጽና ሱዳን ጋር በርካታ ድርድሮች የተካሄዱ ሲሆን ኢትዮጵያ የተፋሰሱ አገራትን ሳትጎዳ የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀምና መብቷን አጠናክራ ትቀጥላለች። ለዚህም ከዚህ ቀደም በግድቡ ላይ አማካሪው ድርጅቱ ያቀረበውን ሪፖርት ላይ በቁ ማብራሪያ እንዲደረግ፣ ያለ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ችግሮችን በድርድር የመፍታትና የመሰረተ ልማት ፈንድ ማቋቋም የሚያስቸል ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።