የምዕራባዊያን ሚዲያዎች ለአሸባሪ የህወሃት ቡድን የወገነ ዘገባ ማሰራጨታቸው የተለመደ ሆኗል

57

ባህርዳር ፤ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) አሜሪካን ጨምሮ የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት ሚዲያዎች ለአሸባሪ የህወሃት ቡድኑ የወገነ ዘገባ ማሰራጨታቸው የተለመደ መሆኑን እያየን ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናገሩ።

"የሀሰት መረጃ በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ  ያሳደረው ጫና" በሚል መሪ ሃሳብ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና  ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጁት  የምክክር ጉባኤ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤  የአንዳንድ ምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሃሰተኛ ዘገባ በማሰራጨት  ኢትዮጵያን ለመጉዳት እየጣሩ ነው።

በተለይም በዚህ የህልውና ዘመቻ ወቅት መንግስት የሀገርና የህዝብን አንድነት ለማስጠበቅ የሚሰራውን ወደ ጎን በመተው ለአሸባሪ ቡድኑ የወገነ ዘገባ  ማሰራጨታቸው የተለመደ መሆኑን እያየን ነው ብለዋል።

አሸባሪ ቡድኑ ግፍና በደል የተፈፀመበትን የአማራና የአፋር ህዝብ ወደ ጎን በመተው ጩኸታቸው ሁሉ ለወራሪው   መሆኑ አሳዛኝ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል።

ይሄን እኩይ ተግባራቸውን የሚፈፅሙትም ሳያውቁ ሳይሆን ሆን ብለው ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የያዙትን ግብ ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ  የሚገኙ ምሁራንም ይሄን እኩይ ድርጊታቸውን በአግባቡ በመገንዘብ እንደዚህ ዓይነት ተከታታይ ጉባኤ በማዘጋጀትና መፍትሄ  በመዘየድ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት በየጊዜው የሚነዛው የሃሰት መረጃ በማህበረሰባችን ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው ብለዋል።

በሚነዛው የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ህብረተሰቡ  ሃብትና ንብረቱን እየተወ በመፈናቀሉ ለተለያዩ ችግሮች  መዳረጉን አውስተው፤  ይሄን እኩይ ድርጊት በጋራ መመከት ይገባል ብለዋል።

በጉባኤው ላይም የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጠቅላላ ሁኔታ፣ ወቅታዊ የሃገሪቱ  ሁኔታ ፣የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ስኬቶችና ተግዳሮቶች፣  የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎችና የአፍሪካ ገጽታ  በሚሉ ርዕሶች ዘሪያ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር እንደሚደረግባቸው ታውቋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ የክብር ዶክተር ኦባንግ ሚቶ፣ የሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተወካዮች፣ የክልሎች የኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ  ሃላፊዎችና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በጉባኤው ላይ እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም