ቀጥታ፡

የአጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ለሕዝብ እይታ ይቀርባል

ጎንደር ፤ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የጎንደር ከተማን ቱሪዝም ለማነቃቃትና የቱሪስት ፍሰቱንም ለመጨመር የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ የአጼ ቴዎድሮስ ሽሩባ (ቁንዳላ) ለህዝብ እይታ እንደሚቀርብ የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አስታወቁ፡፡

እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1868 መቅደላ ላይ አጼ-ቴዎድሮስ ‘ለእንግሊዝ ወታደሮች እጅ አልሰጥም’ ብለው ራሳቸውን እንደሰዉ የታሪክ ድርሳናት ይገልፃሉ።

የአፄ ቴዎድሮስ ቁንዳላም ከ150 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዳያስፖራው ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ወደ ከተማው የሚመጡ እንግዶችን በሚስተናገዱበት ሁኔታ በጎንደር ከሆቴል ባለቤቶች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ዘውዱ ማለደ በወቅቱ እንደተናገሩት፤በከተማው የሚከበረው የጥምቀት በዓል የተቀዛቀዘውን የከተማውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል የሚፈጥር አጋጣሚ ነው፡፡

የቱሪዝም እንቅስቃሴውንና የቱሪስት ፍሰቱን ለመጨመር የአጼ ቴዎድሮስ ሹሩባ (ቁንዳላ) በበዓሉ ወደ ከተማው መጥቶ በሀገር ውስጥና በውጭ ቱሪስቶች እንዲጎበኝ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ቁንዳላው ከበዓሉ ቀደም ብሎ ወደ ከተማው የሚገባበት የክብር አቀባበል ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ጠቁመው፣ ይህም ''ትልቅ የሀገር ቅርስና ታላቅ ኩነት ነው'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር በዓሉን ለማክበር አንድ ዓቢይና ዘጠኝ ንዑሳን ኮሚቴዎች በማዋቀር ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።

በበዓሉ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዳያስፖራዎችና እንግዶች ወደ ከተማው ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።

የከተማውን ሰላምና የእንግዶችን ደህንነት ለማስጠበቅ የከተማው ነዋሪዎችና ወጣቶች የሚሳተፉበት የፀጥታ አደረጃጃት መዋቀሩንም አቶ ዘውዱ ገልጸዋል፡፡

በከተማው በሆቴልና ቱሪዝም ስራ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉና እንግዶቹን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እንግዳ አክባሪነት ተቀብለው እንዲያስተናግዱ አሳስበዋል፡፡

የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ የገናና የጥምቀት በዓላትን በላሊበላና በጎንደር ከተሞች በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአሸባሪው ህወሃት ጉዳት የደረሰበት የላሊበላ አውሮፕላን ማረፊያ በፍጥነት ጥገና ተደርጎለት በዓሉን ለሚያከብሩ ምዕመናንና ዳያስፖራዎች እንዲያስተናግድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ሆቴሎችና የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ባለማድረግ የቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘም ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡

በከተማው የሚገኙ ሆቴሎችና መዝናኛዎች እስከ 3 በመቶ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ እንግዶችን ሊያስተናግዱ ይገባል ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ የሆቴል ማህበራት ፕሬዚዳንት አቶ አማረ አጥናፉ ናቸው፡፡

በመድረኩ የሆቴል ባለቤቶች፣የአማራ ክልልና የከተማው የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም