የኮፓ ኮካ ኮላ አገር አቀፍ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኮፓ ኮካ ኮላ አገር አቀፍ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ተጀመረ
አዲስ አበባ ነሀሴ 20/2010 አራተኛው የኮፓ ኮካ ኮላ አገር አቀፍ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር ትናንት በባቱ ከተማ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያወዳድራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ ከ15 ዓመት በታች ከኮካኮላ ኩባንያ ጋር በመተባበር የሚካሄደው የትምህርት ቤቶች ውድድር ነው። ይህ ውድድር ከሰኔ ወር 2010 ዓ.ም በትምህርት ቤቶች እና በክልል አቀፍ ደረጃ ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ከውድድሮቹ የተመለመሉ ታዳጊዎች ክልል እና የከተማ አስተዳድራቸውን ወክለው ይወዳደራሉ። የእግር ኳስ ውድድሩ ብቃት ያላቸውን ታዳጊ ወጣቶች ለማፍራት የሚያግዝ ነው ተብሏል። በውድድሩ ላይ በሁለቱም ጾታዎች ስምንት ክልሎች በሁለት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ውድድሩ ትናንት በባቱ ከተማ በመክፈቻ ፕሮግራም መጀመሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል። በውድድሩ መክፈቻ ቀን በተደረጉ ጨዋታዎች በወንዶች በምድብ አንድ የኦሮሚያ ክልል የአማራ ክልልን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የአፋር ክልልን በተመሳሳይ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል። በሴቶች በምድብ አንድ የኦሮሚያ ክልል የአዲስ ከተማ አስተዳደርን 3 ለ 1 በሆነ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከአፋር ክልል ጋር ባደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት ተለያይተዋል። ቀጣይ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው የሚካሄዱ ይሆናል። ትግራይ፣ ሶማሌ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በውድድሩ ላይ አልተሳተፉም። አራተኛው የኮፓ ኮካ ኮላ አገር አቀፍ የታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። አገር አቀፍ የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር በ2007 ዓ.ም ሲጀመር ሁለት ሺህ ታዳጊዎች በማሳተፍ የተጀመረ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊ ቁጥሩን በማሳደግ በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ ውድድሩ 45 ሺህ ታዳጊዎች ተሳትፎ እንዳደረጉ ተገልጿል። ባለፉት ሶስት ውድድሮች የተሳተፉ 100 የሚጠጉ ታዳጊዎች ወደ ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ገብተዋል።