የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ

145

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በይዘት፤ በድምጽና ምስል ቀረጻ፣ በአርትኦት እንዲሁም በተቋማዊ ብራንዲንግ ዘርፍ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ።

በሥልጠናው ማጠቃለያ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተባባሪ ሚኒስትርና የኢዜአ የቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ ኢዜአ ትልቅ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ግንባታ ሥራ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

የሀገርን ገጽታ የሚገነቡ፣ የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድሙና ብሄራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን በጥራት መስራት የሚያስችለውን ሪፎርም እያካሄደ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢዜአ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ከፍ የሚያደርግ የገጽታ ግንባታ ሥራ እየሰራ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቢቂላ፤ ከ14 ተቋማት ለተውጣጡ ሙያተኞች በተቋሙ የተሰጠው ሥልጠናም ''እንደ ሀገር እኛ አንድ ነን፤ አጀንዳችንም ተመሳሳይ ነው'' የሚል መልእክት ያዘለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ስልጠናው አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ ውስጥ አጀንዳ በመቅረጽ ረገድ ምን ላይ ነው መተኮር ያለበት የሚለውን የመለሰ ነው ብለዋል።

ስልጠናው በተግባር የተደገፈ መሆኑ ሰልጣኞች በቀጣይ በየተቋሞቻቸው የሚሰሯቸውን ስራዎች በብቃት መፈጸም እንዲችሉ ያግዛል ብለዋል።

ሰልጣኞቹም በቆይታቸው የተሻለ እውቀት ማግኘታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ በየተቋማቸው የተሻለ ሥራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በሚያውቋቸው ነገሮች ላይ ተጨማሪ እውቀት መገብየታቸውንም ገልጸዋል።

ሥልጠናው ከታህሳስ 4 እስከ 15 ቀን 2014 ዓ.ም በጉዳዩ ላይ የተሻለ እውቀት ባላቸው ምሁራንና ሙያተኞች የተሰጠ ነበር።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣ _

ወደ ግንባር ዝመት፣_

መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም