የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለማረጋገጥ የኢኮኖሚ አቅምን ማጠናከር አስገዳጅ ነው

50

ታህሳስ 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ነጻነት ለማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ አቅምን ከሀገሪቱ ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ሀገር አቀፍ የትምህርት ቤት ቦርሳና ዩኒፎርም ፕሮጀክት መተግበር የሚያስችል ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ የሀገር ውስጥ ባንዳዎችና የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ለመቋቋም የሀገር ውስጥ ምርትን መጠቀም አስገዳጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች አምራቾች በተለያዩ ምክንያቶች ከማምረት አቅማቸው በግማሽ ማምረታቸውን ገልጸዋል ሚኒስትሩ።

በመሆኑም ሀገሪቱ የገጠማትን ሁሉን አቀፍ ጦርነት ለማሸነፍ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመግዛት ኢንዱስትሪውን ማነቃቃት የዜግነት ሀላፊነት ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአንዳንድ ምዕራባዊያንን ሴራ ለመቋቋም መንግስት ከሚወስዳቸው የመፍትሄ አቅጣጫዎች ባልተናነሰ የሕብረተሰቡ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያን ታሪካዊና መልክዓ ምድራዊ ሀብት በመጠቀም "ድህነትን ባለማሸነፋችን ለአንዳንድ ምዕራባዊያን ሴራ ተጋልጠናል" ብለዋል።

በኢኮኖሚ የደቀቁ ሀገራት ያንሰራሩት የህዝብና የመንግስት ቁርጠኝነትን በማጣመራቸው እንደሆነ ያብራሩት አቶ መላኩ፥ በኢትዮጵያም የተፈጠረው ሀገራዊ መነቃቃት 'ለእድገታችን ተጨማሪ ዕድል ነው' ብለዋል፡፡

ሀገር አቀፍ የተማሪዎች አልባሳትና ጫማዎች ፕሮጀክትም አምራች ሀይሉ ምርቱን ከማስተዋወቅና የስራ ዕድል ከማስፋት ባለፈ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፈንታ ማንደፍሮ የፖለቲካውን ጫና መቋቋም የሚቻለው የግል አንቀሳቃሹን ከመንግስት ጋር በማቀናጀት ሲሰራ መሆኑን አስገነዝበዋል።

በአምራች ሀይሉ ቀደም ሲል ይስተዋል የነበረውን የተሳሳተ የትርፍ እሳቤ በማስተካከል የመንግስትን ሀገር የማዳን ጥሪ ተቀብሎ በአነስተኛ ትርፍ ወገኖቹን ማገልገል እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የተማሪዎች ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ መተካቱ የውጭ ምንዛሬን ከመቆጠብ አልፎ ተማሪዎች የምርት ጥራት ተወዳዳሪነትን በተግባር የሚማሩበት ዕድል እንደሚያሰፋ ጠቁመዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ምገባ ኤጀንሲ ሀላፊ ወይዘሮ አንቺነሽ ተስፋዬ የሀገርን ምርት መጠቀም በሀገር ምርት ከመኩራት ባሻገር የኢትዮጵያን የውስጥ አቅም የምናሳይበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮግራሙ የተማሪዎችና የወላጆችን ማኅበራዊ ችግር በመቅረፍ ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ያግዛል ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሀላፊ ቢረጋ ብርሀኑ ናቸው።

ለፕሮግራሙ ውጤታማነት በአዲስ አበባ የተገኘውን ጥንካሬና ድክመት በመገምገም በክልሎች በሙከራ ደረጃ ለመተግበር ያግዛልም ብለዋል፡፡

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም