በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማትን በመጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሸባሪው ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው የጤና ተቋማትን በመጠገን ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ ነው
ባህር ዳር ፤ ታህሳስ 15/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ጉዳት ያደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በመጠገን አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
ሙሉቀን አያሌው አስመጭና ላኪ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን 150 የሰውነት ሙቀት መጠን መለኪያ መሳሪያዎችን ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ ዛሬ በባህርዳር ድጋፍ አድርጓል።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ ዶክተር ጋሹ ክንዱ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት ፤እንዳሉት አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈፀመባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማትን ያወደመ ሲሆን መድሃኒቶችን፣ የላቦራቶሪ ቁሶችና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎችን ዘርፏል።
እንደ ዶክተር ጋሹ ገለጻ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ በመጠገንና በመገንባት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ዛሬ በአቶ ሙሉቀን አያሌው አስመጪና ላኪ አማካኝነት የተደረጉ ድጋፎች የጤና ተቋማቱን መልሶ ወደስራ ለማስገባት በሚደረገው ጥረት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።
በህወሓት የተዘረፉና የወደሙ የሕክምና ተቋማት መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ባለሀብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፉን የሰጠው ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አያሌው በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ለህልውና ዘመቻው የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።
አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች የደረሰውን ውድመት ለመደገፍ ሰው መሆን ብቻ በቂ ስለሆነ ከባለሀብቱ በተጨማሪ ሁሉም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም አመልክተዋል።