"ወደ አገር ቤት ለሚመጡ እንግዶች የዋጋ ቅናሽ አድርገናል'' - ኢዜአ አማርኛ
"ወደ አገር ቤት ለሚመጡ እንግዶች የዋጋ ቅናሽ አድርገናል''
ባህር ዳር (ኢዜአ) ታህሳስ 15/2014 በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪ መሰረት ለበዓሉ ከውጭ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለሚሰጡ አገልግሎቶች የ40 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ማድረጋቸውን በባህር ዳር ከተማ የሚገኙ ሆቴሎች አስታወቁ።
ወደ ባህር ዳር ከተማ የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ምቹና ተገቢ መስተንግዶ እንዲያገኙ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ተደርጎ መግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የሰመርላንድ ሆቴል ባለቤት አቶ ቢኒያም ኪዳኔ ለኢዜአ እንደገለጹት በልዩ ሁኔታ ጥሪ ተደርጎላቸው ወደ እናት አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን ተቀብሎ ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል።
እንግዶች በሚቀርብላቸው ሁሉን አቀፍ መስተንግዶ ረክተው እንዲሄዱ ለሆቴሉ ሠራተኞች የማነቃቂያ ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል።
እንግዶቹን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል ለመቀበል ከተደረገው ዝግጅት በተጨማሪ ለአልጋና ለሌሎች አገልግሎቶች ከዚህ ቀደም ይከፈል ከነበረው ዋጋ የ40 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ተናግረዋል።
"የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሀገር ቤት ለሚመጡ እንግዶች ቅናሽ ሲያደርግ ሆቴሎች በተወሰነ ፐርሰንት ቀንሰን ውድ የኢትዮጵያ እንግዶችን ማስተናገድ አይከብደንም" ብለዋል።
"በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተደረውን ጥሪ ተቀብለው ሲመጡ ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ደጋግመው እንዲመጡ የሚያደረግ መስተንግዶ ያስፈልጋቸዋል" ያሉት አቶ ቢኒያም፣ ሆቴላቸው ይህንን ከግምት ያስገባ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
"አገር አቀፍ ጥሪውን ተቀብለው ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን ተቀብሎ ጥሩ ቆይታ እንዲኖራቸው ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች እየተሰሩ ነው'' ያሉት ደግሞ በባህር ዳር ከተማ የብሉ ናይል ሪዞርት ሆቴሎች ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው።
እንግዶቹ ጥሩ መስተንግዶ አግኝተውና ረክተው እንዲመለሱ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ በአልጋ ዋጋ ላይ ከዚህ ቀደም ከነበረው የ40 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ተናግረዋል።
አቶ ሰለሞን እንዳሉት ለእንግዶች የተመቻቸው የተሻለ መስተንግዶና የዋጋ ቅናሽ የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም ፋይዳው የጎላ ነው።
ከታህሳስ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት ለእንግዶች ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው።
ወደ ከተማዋ ለሚመጡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አስፈላጊውና ተገቢውን መስተንግዶ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ላይ መደረሱን ገልፀዋል።
የአስጎብኚ ድርጅቶችና የሆቴል ማህበራት እንግዶችን በጥሩ መስተንግዶ እንዲቀበሉ የሚያስችል ዝርዝር እቅድ ወጥቶ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።
"የከተማዋ ፀጥታ ከምንጊዜውም በላይ የተጠበቀ እንዲሆን እየተሰራ ነው" ያሉት ዶክተር ድረስ፣ ፀጥታውን አስተማማኝ ለማድረግ አደረጃጀቶችን በማጠናከር ስምሪት መሰጠቱን ገልጸዋል።
"ትርፍ የሚገኘው በብዙ ነገር ነው" ያሉት ዶክተር ድረስ፣ "የአገር ኢኮኖሚ እንደገና እንዲያንሰራራ አንድ እንግዳ ሲመጣ በእሱ ላይ ዋጋ መጨመር ሳይሆን ነገ ተጨማሪ እንግዳ ይዞ እንዲመጣ የሚያደርግ ምቹ መስተንግዶ መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከዋጋ ጭማሬ ይልቅ በቅናሽ ዋጋ የተሻለ መስተንገዶ በመስጠት ቀጣይ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያስችል መስተንግዶ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የጣና ገዳማትን ጨምሮ ሌሎች ታሪካዊና ተፈጥሯዊ የመስህብ ስፍራዎችን ተዘዋውረው እንዲጎበኙ የሚደረግ መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ አስታውቀዋል።