የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሴካፋ ውድድር የፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ ነሀሴ 20/2010 በታንዛኒያ እየተካሄደ ባለው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ (ሴካፋ) የማጣሪያ እግር ኳስ ውድድር የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኡጋንዳ አቻው ጋር የፍጻሜ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል። ከነሐሴ 4 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ክፍለ አህጉሩን ወክሎ የሚሳተፈው ቡድን ለመለየት ሲካሄድ የነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ይጠናቀቃል። የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት ከኡጋንዳ አቻው ጋር በታንዛኒያ ብሔራዊ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል። በተመስገን ዳና የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ በግማሽ ፍጻሜው ከሩዋንዳ ጋር ባደረገው ጨዋታ በመደበኛ ሰዓት ሁለት አቻ ተለያይቶ በመለያ ምት 4 ለ 2 በማሸንፍ ለፍጻሜ ማለፉ ይታወሳል። የተጋጣሚው የኡጋንዳ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በግማሽ ፍጻሜው አዘጋጇ ታንዛንያ 3 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ለፍጻሜ ደርሷል። ቀይ ቀበሮዎቹ የሚል ስያሜ የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በታንዛኒያ እያሳየ ያለው ብቃት አድናቆት አስችሮታል። ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ የፍጻሜውን ጨዋታ ካሸነፈ በ2011 ዓ.ም በታንዛኒያ በሚካሄደው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ክፍለ አህጉሩን(ሴካፋን) ወክሎ ይሳተፋል። ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ከቀኑ 8 ሰዓት በታንዛኒያ ብሔራዊ ስታዲየም አዘጋጇ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የማጣሪያ ውድድሩ በሰባት ዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድ ሲሆን አሸናፊ የሚሆኑት ሰባት ብሔራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች የእግር ኳስ ውድድር ተሳታፊ ይሆናሉ። እስካሁን በሁለት ዞኖች ያሉ የማጣሪያ ውድድሮች የተጠናቀቁ ሲሆን በማዕከላዊ ዞን ካሜሮን በደቡብ ዞን አንጎላ በአፍሪካ ዋንጫው መሳተፋቸውን አረጋግጠዋል።