እንዳሻው አላዩ ከዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ውጭ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
እንዳሻው አላዩ ከዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ውጭ ሆነ
አዲስ አበባ ነሃሴ 20/2010 በሀንጋሪ ርዕሰ መዲና ቡዳፔስት እየተካሄደ በሚገኘው ስድስተኛው የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የተሳተፈው እንዳሻው አላዩ ከውድድሩ ውጭ ሆኗል። የቦክስ ውድድሩ ከነሐሴ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ይገኛል። እንዳሻው በ49 ኪሎ ግራም በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ኢኳዶራዊውን ጆናታን ሜርቻንና አርሜንያዊውን ዩጊኪያን ማሸነፉ ይታወሳል። ትናንት ማምሻውን በሩብ ፍጻሜው ከፖርቶ ሪኮ ተወዳዳሪ ሪቬራ ፒዛሮ ጋር ጨዋታውን አድርጎ በነጥብ በመሸነፉ ምክንያት ከውድድሩ ውጭ መሆኑን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። በጨዋታው ወቅት እንዳሻው እጁ ላይ ጉዳት እንዳጋጠመው ተናግረዋል። በሌላ በኩል 48 ኪሎ ግራም ኢትዮጵያን ወክላ የተጫወተችው ሀና ደረጀ በመጀመሪያ ጨዋታዋ በአሜሪካዊቷ ሳንድራ ቶቫር ተሸንፋ ከውድድሩ ውጭ መሆኗን አስታውሰዋል። የዓለም የወጣቶች የቦክስ ውድድር እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።