ድሬዳዋ ለቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ተዘጋጅታለች

68

ድሬዳዋ ፤ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደርና ህዝቡ ለቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል የሚመጡ ዲያስፖራዎችና ሌሎችንም እንግዶች ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ።

የአስተዳደሩ ከንቲባ  ከድር ጁሃር  በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ፤ድሬዳዋ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ የሰፈነባት ናት።

በዚህም አስተዳደሩና ህዝቡ ለቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ የድሬዳዋ ተወላጆች ወዳጆችና ዲያስፖራዎችንና ሌሎችንም እንግዶች ተገቢውን አቀባባልና መስተንግዶ  እንደሚያዳርጉ  ገልጸዋል።

"እንግዶችን በሰላም ተቀብለን በሰላም እንዲመለሱ ዝግጅትም ተጠናቋል" ብለዋል ከንቲባው።

የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው፤ የፀጥታ አካላት የዘንድሮ የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጅት ማድረጋቸውን ነው የተናገሩት፡፡

የድሬዳዋ፣ የሐረሪ፣ የምስራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ የፌደራል ፖሊስ፣ ሚሊሻና ብሔራዊ ደህንነት ለበዓሉ ሰላምና ደህንነት መጠበቅ  ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከውጭ ወደ ሀገርቤት የሚገቡትንና ለበዓሉ ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚመጡትን እንግዶች ህዝቡ በተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህል እንዲያስተናግድም ኮሚሽነር አለሙ ጥሪ አቅርበዋል።   

ታህሳስ 19  በሚከበረው  የቁሉቢ ገብርኤል  የንግስ በዓል ለመታደም  ምዕመናን፣ ቱሪስቶች፣አምባሳደሮች እና ዲያስፖራዎች እንደሚመጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም