በአማራ ክልል ከ313 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከ313 ሺህ በላይ ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቄያቸው ተመልሰዋል
ባህር ዳር ታህሳስ 15/2014 (ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ቡድን ከተፈናቀሉት ውስጥ እስካሁን ከ313 ሺህ በላይ ወገኖች ወደ ቄያቸው መመለሳቸውን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አሸባሪ ቡድኑ በክልሉ በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች በርካታ በደል ፈፅሟል።
ቡድኑ ንፁሃንን ከመግደልና ከማሰቃየት ባለፈ ንብረት በመዝረፍና በማውደም የህዝብ ጠላትነቱን በተግባር አሳይቷል ብለዋል።
በወረራ በቆየባቸው አካበቢዎችም ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ከቤት ንብረቱ በማፈናቀል ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ ማድረጉን አስረድተዋል።
ከ7 ሚሊዮን የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ አካባቢያቸውን ሳይለቁ በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው መቆየታቸውንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በአሸባሪ ቡድኑ ተይዘው የቆዩ የክልሉ አካባቢዎች ነፃ እንዲወጡ መደረጉን አውስተዋል።
አካባቢዎቹ ነፃ መውጣታቸውን ተከትሎም በደብረ ብርሃን፣ ሞጣ፣ መካነ ሰላም፣ ባህር ዳር፣ እብናትን ጨምሮ በሰባት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድና ከህብረተሰቡ ጋር ተጠግተው የቆዩ ተፈናቃይ ወገኖች ወደቄያቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እስከሁን በተደረገው ጥረት 163 ሺህ ተፈናቃዮች መንግስት ትራንስፖርት በማመቻቸት፤ ከ150 ሺህ የሚበልጡት ደግሞ በራሳቸው መመለሳቸውን አስታውቀዋል።
የተመለሱትም በአብዛኛው መጠለያ ያላቸው ሲሆኑ የተጎዳባቸውም ባሉበት መልሶ ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።
የቀሩ ተፈናቃዮችንም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደቀደመ ቀያቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ እያሱ ፤ ተመላሾች የዕለት ምግብ ይዘው እንዲሄዱም ድጋፍ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሰሜን ሸዋ፣ ሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ዋግ ህምራና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች ወደ ቄያቸው ለተመለሱና ችግሩን ተቋቁመው በአካባቢያቸው ለቆዩ ወገኖችም 82 ሺህ 942 ኩንታል የዕለት ምግብ እህል በማከፋፈል ድጋፍ መደረጉንም ጠቅሰዋል።
በክልሉ በተቋቋሙ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለው ለቆዩ ወገኖችም እስካሁን 340 ሺህ ኩንታል የዕለት ምግብ እህል ድጋፍ በማድረግ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚበልጥ ህዝብ ማሰራጨት መቻሉን አስታውሰዋል።
ህዝቡን መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ ተዘጋጅቶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ችግሩን ለመሻገር የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ እያሱ፤ የመልሶ ማቋቋም ተግባሩን መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ባለሃብቱና ህብረተሰቡ በመደገፍ ርብርብ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።