ኦሚክሮን የተሰኘው የኮቪድ-19 አዲሱ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰት አለመከሰቱን ለማረጋገጥ ምርምር እየተካሄደ ነው

70

ታህሳስ 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኦሚክሮን የተሰኘው የኮቪድ-19 አዲሱ ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰት አለመከሰቱን ለማረጋገጥ ናሙና በመውሰድ ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሥርጭት ምጣኔና የወረርሽኙን ሁኔታ በሚመለከት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 የሥርጭትና የሞት ምጣኔ እየጨመረ በመምጣቱ የማህበረሰቡ የጤና ስጋት ከመሆን አልፎ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በአገሪቱ እስከ ትናንት ድረስ ከ4 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የኮቪድ-19 ምርመራ የተደረገ ሲሆን፤ 382 ሺህ ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የዓለም የጤና ድርጅት ህዳር 17 ቀን 2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ኦሚክሮን የተባለ አዲስ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ መከሰቱን ይፋ ማድረጉን ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

ይህም ቫይረስ በከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨት በሁለት ወራት ውስጥ በ106 ሀገራት መገኘቱንም አብራርተዋል።

መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ያብራሩት ሚኒስትሯ ኦሚክሮን ቫይረስ በፍጥነት የሚዛመት ከመሆኑ ባሻገር ከዚህ ቀደም በኮቪድ-19 ተይዘው የነበሩ ሰዎችንም ጭምር በፍጥነት የሚያጠቃ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሁለት ሳምንት ወዲህ የኮቪድ-19 ምጣኔ በተከታታይ የጨመረ ሲሆን፤ ከነበረበት ሦስት በመቶ ወደ 28 በመቶ አድጓል ነው ያሉት።

ይህንን መነሻ በማድረግም ኦሚክሮን የተሰኘው የኮቪድ-19 ዝርያ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰት አለመከሰቱን ለማረጋገጥ ናሙና በመውሰድ ምርምር እየተካሄደ ይገኛል።

ለኮቪድ ፕሮቶኮል ተብለው የወጡ የመከላከያ መርሆዎችን በአግባቡና በጥንቃቄ መተግበርና የሥርጭቱን መጠን መቀነስ የግድ ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ የመከላከያ ዘዴ ኦሚክሮን የተሰኘውን አዲሱን የኮቪድ-19 ዝርያ ለመከላከልም ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ ሚኒስትሯ አክለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም