በአማራ ክልል ተጥሎ የነበረው የሰዓት ገደብ ተሻሻለ

55

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ያለውን አንጻራዊ ሰላምና የኢኮኖሚ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በክልሉ ተጥሎ በነበረው የሰዓት ገደብ ላይ ማሻሻያ መደረጉን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደስራ እንዲመለሱ የሚለውን ጨምሮ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን ማስቀመጡም ተመልክቷል።

የቢሮ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት የክልሉ አብዛኛው አካባቢዎች ከወራሪው ህወሓት ቡድን ነጻ በመውጣታቸው፣ የአካባቢ መስተዳድሮችን ማቋቋም በመቻሉ፣ ኢኮኖሚያዊ ጫናን ለመቀነስ እና በሌሎች ምክንያቶች በክልሉ ተጥሎ የነበረው የሰዓት ገደብ ተሻሽሏል።

በዚህም ምሽት እስከ 2 ሰዓት የነበረው የሰዓት ገደብ እንቅስቀሴ ወደ 4 ሰዓት የተራዘመ ሲሆን ከጧቱ 12 ሰዓት የነበረውም ወደ 11 ሰዓት ተኩል ዝቅ እንዲል ምክር ቤቱ መወሰኑን አስታውቀዋል።

የሰዓት ገደብ መሻሻሉ በቀጣይ የገና በዓልን በላል ይበላ፤ ጥምቀትንም በጎንደር በድምቀት ለማክበር ከተያዘው ዕቅድ ጋር ተያይዞ ተገቢነት ያለው መሆኑንም አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በአሸባሪው ህወሓት በወረራ ተይዘው በነበሩና በቅርቡ ነጻ በወጡ አካባቢዎች የተሻሻለው የሰዓት ገደብ ኮማንድ ፖስቱ እየገመገመ በሚወስነው መሰረት የሚፈጸም መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

ሃላፊው አያይዘው እንደገለጹት የሥራ ማስኬጃ በጀታቸውን ለህልውና ዘመቻው እንዲያውሉ ተወስኖባቸው የነበሩ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ወደ መደበኛ ሥራቸው እንዲመለሱ ተወስኗል።

በእዚህም በየደረጃው የሚገኙ የሥራ ሃላፊዎችም ከዛሬ ጀምሮ ሠራተኞቻቸውን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በማወያየትና መግባባት በመፍጠር ወደ ሥራ በማስገባት ለህዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አብዛኛው በጀታቸውን ለህልውና ዘመቻው ከመዋሉ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን የበጀት ችግር ለመቀነስ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ እቅዳቸውን በመከለስና ከበጀታቸው ጋር በማጣጣም ወደ ስራ እንዲገቡ አስገንዝበዋል።

አቶ ግዛቸው እንዳሉት ውሳኔው ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት በጦርነቱ ተቀዛቅዞ የነበረውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማንሰራራት ያስችላል።

በህልውና ትግሉ በጠላት ላይ ርምጃ በመውሰድ አኩሪ ጀብድ ለፈጸሙ የጸጥታ አባላትና ግለሰቦች እውቅና የሚሰጥበት ስነ ስርዓት እንደሚዘጋጅም አቶ ግዛቸው በመግለጫው አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አካባቢዎች ነጻ ከመውጣታቸው ጋር ተያይዞ እየታየ ያለው ተኩስ ትክክልና ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው መንግስት ድርጊቱን በሚፈጽሙ ግለሰቦች ላይ እርምጃ  እንደሚወስድ አቶ ግዛቸው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም