ከፓርኩ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኘ

49

ድሬዳዋ፤ ታህሳስ 14/2014 (ኢዜአ) ከድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ውጭ ከተላኩ ምርቶች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ መገኘቱን የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሒም አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኢንዱስትሪ ፓርኩን ጎብኝተው በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚያስተዋውቅ መርሀግብር እንደተዘጋጀም ተመላክቷል፡፡

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ እንዳሉት፤ በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶችን ተረክበው ወደሥራ የገቡ ሦስት ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ወደ ውጭ  መላክ ከጀመሩ ሁለት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡

በነዚህም  ባለፉት 5 ወራት ወደተለያዩ የአውሮፓና አፍሪካ ሀገራት ከተላኩት የቆዳ ጫማዎች፣ድርና ማግ እንዲሁም የሲሚንቶ ማሸጊያ ከረጢቶች ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

ምርቶቹ ከተላከባቸው ሀገራት መካከል ኢጣልያ፣ ቻይና ፣ ፓኪስታን እና ጂቡቲ  እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከምርት ሽያጭ በተጨማሪ ከሼዶቹ ኪራይም 12 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ነው ያመለከቱት።

እንደ አቶ ካሚል ገለፃ፤ሥራ በጀመሩት ፋብሪካዎች ውስጥ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተመረቁ 3 ሺህ ወጣቶችና የአካባቢው ማህበረሰብ የሥራ ዕድል አግኝተዋል፡፡

በቅርቡ "ኤል አውቶ" የተባለ የመኪና መገጣጠሚያ ኩባኒያ በፓርኩ ውስጥ ሁለት ሼዶች ተረክቦ ሥራ ለመጀመር በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም አቶ ካሚል ጠቁመዋል፡፡

ሌሎች የውጭ  ባለሃብቶችም በፓርኩ ውስጥ ገብተው ሥራ ለመጀመር ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት የሚገቡ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ኢንዱስትሪ ፓርኩን ጎብኝተው በዘርፉ እንዲሳተፉ የሚያስተዋውቅ መርሀግብር እንደተዘጋጀም የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ  ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ ሼድ ተረክቦ የሲሚንቶ ከረጢቶችን በማምረት ላይ የሚገኘው ፋብሪካ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈረሃን ሣሊህ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ከረጢቶቹ በሀገር ውስጥ በመመረታቸው ቀደም ሲል ከውጭ ሲገዙ የነበሩ ምርቶች በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አግዟል፡፡

"እኔና ጓደኞቼ ሌሎችን አካተን ከአሜሪካ አትላንታ መጥተን ሥራ ከጀመርን ሁለት ዓመት ሆኗል፤ ለ200 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረናል፤ ሥራውን እያስፋፋን ስለሆነ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

"የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከጅቡቲ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ ከመገኘቱ ባለፈ የባቡር ትራንስፖርትን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ-ልማቶች ቢሟሉለትም በፓርኩ ውስጥ የውሃ ችግር አለ" ነው ያሉት።

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ባለሃብቶች እና ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራዎች ወደፓርኩ እንዲመጡ ከተፈለገ መንግስት የፓርኩን የውሃ ችግር መፍታት እንዳለበትም አመልክተዋል።

በተጨማሪ ከድሬዳዋ ከተማ ወደፓርኩ መምጫ ላይ ግንባታው የተጓተተው የአስፓልት መንገድ በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሚል ኢብራሂም በበኩላቸው የውሃ ችግሩን ለመፍታት የተጀመሩት የውሃ ፕሮጀክቶች በመጠናቀቃቸው በሚቀጥለው ወር ችግሩ ሙሉ በሙሉ እንደሚፈታ አረጋግጠዋል።

"የመንገዱን ችግር ከድሬዳዋ ከንቲባና ከፌደራል መንገዶች ባለስልጣን ጋር ውይይት ተደርጎ የጋራ መግባባት ላይ በመደረሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሄ ይሰጠዋል" ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም