በጦርነቱ የተጎዳው ኢኮኖሚ እንዲያገግም የምጣኔ ሃብት ምሁራን እገዛ ያስፈልጋል

39

አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) በጦርነቱ ሳቢያ የተጎዳው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ሙያዊ እገዛ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተጠቆመ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ "የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ከየት ወዴት" በሚል ርዕሰ ጉዳይ በርካታ ምሁራን የተሳተፉበት ውይይት አካሂዷል።

የውይይት መነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት አንጋፋው የምጣኔ ሃብት ምሁር ዶክተር በፈቃዱ ደግፌ፤ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ታሪክ፣ አሁን እና በቀጣይ ትኩረት በሚሻው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር፣ አምራች ዘርፉን ተወዳዳሪ ማድረግ፣ በምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ሳቢያ የሚደረግ የውጭ ጣልቃ ገብነትን መቋቋም የሚያስችሉ መንገዶችንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ በየትኛውም የታሪክ አጋጣሚ የጎዳችው አገር የለም ያሉት ዶክተር በፈቃዱ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ሲሉ ያልተገባ ጫና የሚያደርጉባት ግን ጥንትም እስከ አሁንም አሉ ብለዋል።

በመሆኑም ምሁራን በአገራቸው ላይ የሚደረገውን ጫና ለመቋቋም በሙያቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና ለፖሊሲ የሚሆኑ የጥናት ግኝቶችን እንዲያቀርቡ ጠቁመዋል።

ዶክተር በፈቃዱ የዓለምን የምጣኔ ሃብት አካሄድ በማውሳትና አሁን ያለውን የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት አካሄድ በመዳሰስ ቀጣይ አቅጣጫዎች ያሏቸውንም አመላክተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የምጣኔ ሃብት ምሁራንም አሸባሪው ህወሓት በአገር ህልውና ላይ የከፈተው ጦርነት ያመጣው ኪሳራ በጥናት ተደግፎ መስተካከል የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።  

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ኃይሉ ኤልያስ፤ ጦርነቱ በምጣኔ ሃብት ላይ ካስከተለው ጉዳት እንዲያገግም የዘርፉ ምሁራን ተሳትፎና ሙያዊ እገዛ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

መሰል ችግሮች ያጋጠማቸው አገራት ከደረሰባቸው የምጣኔ ሃብት ድቀት አገግመው ወደ እድገትና ብልጽግና የሄዱበትን መንገድ በማጥናት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።

በጦርነቱ የተጎዳው ምጣኔ ሃብት እንዲያገግም ከማገዝ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርናን ማዘመን ይጠበቃል ያሉት ደግሞ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር አሰፋ አድማሴ ናቸው።

ዶክተር ኃይሉ ኤልያስም ኢትዮጵያ ከገጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ እንድትወጣ በየዘርፉ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ሙያዊ እገዛ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል ።

ምሁራኑ ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር ወጥታ በምጣኔ ሃብት የምታገግምባቸው ያሏቸውን ምክረ ሀሳቦችም አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት በዘላቂነት ለማሻገር በትምህርት ስርዓቱ፣ በምርምር እንዲሁም በዘመናዊ አሰራር በመታገዝ መከወን እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን ክብሯ እንደተጠበቀ የምትቀጥልና የማትደፈር ለማድረግ መንግስት፣ ምሁራን፣ የግሉ ዘርፍና መላው ኢትዮጵያዊያን በጋራ መቆም አለብን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም