ለውጡን የሚደግፉም የሚቃወሙም ኃይሎች በሁሉም የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ አሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ - ኢዜአ አማርኛ
ለውጡን የሚደግፉም የሚቃወሙም ኃይሎች በሁሉም የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ አሉ-ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ
አዲስ አበባ ነሐሴ 19/2010 በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ የሚደግፉም የሚቃወሙም ኃይሎች በሁሉም የኢህአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እህት ድርጅቶች ለውጡን በምን ያህል ደረጃ ተቀብለውታል? ሁሉም እኩል ነው ወይ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ሙሉ ለሙሉ ለውጥ የተቀበለና ያልተቀበለ ድርጅት አለመኖሩን ገልጸዋል። ለውጡ በግለሰቦች የተወሰነ መሆኑን ጠቁመው በሁሉም ድርጅቶች ውስጥ ለውጡን ደግፈው የቆሙ ኃይሎች የመኖራቸውን ያህል የማይደግፉ ኃይሎች እንዳሉ ሊታወቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ከስልጣን የተነሱና ጡረታ የወጡ አንዳንድ ሰዎች ማኩረፋቸውንና ለውጡን ለመቀበል የተቸገሩ እንዳሉም ተናግረዋል። ትናንሽ ነገሮችን እያነሱና እያጋነኑ ክፍተት ለመፍጠር የሚደረገውን ሙከራ በማክሸፍ ለውጥ ፈላጊውን ኃይል እያበራከቱ መሄድ የሚያስፈልግ እንደሆነም ገልጸዋል። ህወሃትን ለውጥ የማይቀበል ድርጅት አድርጎ መውሰድ የተሳሳተ እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። ኢህአዴግ በሃሳብ ተከራክሮ መሸነፍ የሚቻልበትን አውድ ለማስፋት ለመስራት ዝግጁነት ያለው እንደሆነም ጠቁመዋል። ሁሉም ኢትዮጵያ የአገሩ ባለቤት እንደሆነ አምኖ የሚንቀሳቀስበት አውድ እንዲፈጠርም ኢህአዴግ የሚሰራ እንደሆነ አመልክተዋል። እኔ ከሌለሁ ኢትዮጵያ የለችም የሚል ሃሳብ ይዞ ስልጣን ላይ መቆየት የማያዋጣ መሆኑንም ገልጸዋል። ኢህአዴግ አገራዊ ለውጥን ለማምጣት ብዙ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱንም አስታውሰዋል።