“የሰው ዘር መገኛና የአፍሪካውያን ቤት ወደሆነችው ኢትዮጵያ በመግባት አፍሪካዊያን በጋራ መቆማችንን ማሳየት አለብን”

72

ታህሳስ 14/2014/ኢዜአ/ የሰው ዘር መገኛና የአፍሪካውያን ቤት ወደሆነችው ኢትዮጵያ በመግባት አፍሪካዊያን በጋራ መቆማችንን ማሳየት አለብን ሲሉ የዩጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል ተናገሩ።

የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት እንግባ ጥሪ አንዳንድ ምዕራባውያን እንደሚሉት ሳይሆን ኢትዮጵያ የሰላም አገር መሆኗን የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር ነውም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በውጭ አገር የሚኖሩ አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት እንዲመጡ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የዩጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ሊቀ-መንበር ዶክተር ሩጋራማ ዳንኤል የምዕራቡ ዓለም አገራትና መገናኛ ብዙሃኖቻቸው ኢትዮጵያ የደህነት ስጋት ያለባት አገር ናት በማለት ዓለምን ለማሳሳትና በዜጎች ላይ ፍርሃት ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ምዕራባውያን አገራት ዜጎቻቸው እንዲወጡ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ሲያቀርቡ እንደነበረ አስታውሰዋል።

አፍሪካውያን ወደ እናታቸው ቤት መጥተው በመሰባሰብ አፍሪካውያን አንድ ቤተሰብና ማህበረሰብ መሆናቸውን በተግባር በማሳየት ጠላቶቻችንን ማሳፈር ይጠበቅብናል ብለዋል።

እሳቸውን ጨምሮ የዩጋንዳ የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ አባላት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡና ሌሎች የዩጋንዳ ዜጎች ጥሪውን እንዲቀላቀሉ የማስተባበር ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ ሊቀ-መንበሩ አመልክተዋል።

አፍሪካውያንና በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ወዳጆች ጥሪውን ተቀብለው በመምጣት የምዕራባውያን አገራትን ሴራ ማክሸፍ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ሩጋራማ የገለጹት።

የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ አፍሪካውያን የአፍሪካ ማዕከልና የሰው ዘር መገኛ ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ መምጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ጥሪው የዓለም ማህበረሰብ ተቀብሎት ሊቀላቀለው የሚገባ መልካም ሀሳብ እንደሆነም ዶክተር ሩጋራማ አክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዳያስፖራዎች ቢያንስ አንድ የውጭ አገር  ዜጋ ወደ ኢትዮጵያ ይዘው እንዲመጡ ጥሪ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም