የውጭ ግንኙነት የውስጥ ጥንካሬ ነፀብራቅ በመሆኑ የውስጥ ሰላምን ማስጠበቅ ላይ በትኩረት ይሰራል

97

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2014(ኢዜአ) የውጭ ግንኙነት የውስጥ ጥንካሬ ነፀብራቅ በመሆኑ የውስጥ ሰላምን ማስጠበቅ ላይ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለፁ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ “ህልውናን መጠበቅ፣ ዕድገትን ማዝለቅ” በሚል ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ አሸባሪው ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ በከፈተው ጦርነት ምክንያት ዲፕሎማሲው በተወሳሰበ ሁኔታ ውሰጥ ሆኖ እያለፈ መሆኑን አንስተዋል።

አንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ድብቅ አጀንዳ በመያዝ በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ሀሰተኛ ዘገባዎችን እያሰራጩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያዊያን አንድ በመሆናቸው ከውጭና ከውስጥ ያለውን ግፊት ሊቋቋሙ መቻላቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየተስተዋለ ያለው ጫና በመላ አፍሪካ ላይ የሚደርስና እየደረሰ ያለ ጫና እና ጣልቃ ገብነት በመሆኑ አፍሪካዊያን ለኢትዮጵያ ድጋፋቸውን ማሳየታቸውንም አድንቀዋል።

በመሆኑም የውጭ ግንኙነት የውስጥ ጥንካሬ ነፀብራቅ በመሆኑ የውስጥ ሰላምን በማስጠበቅ ጠንካራ ዲፕሎማሲ እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም