የዲላ ኢንዱስትሪ ፓርክን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው

ዲላ፣ ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክን በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቁ።

የጀርመን ቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ለፓርኩ 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ሁለት የከባድ ዕቃ ማንሻዎችና ሌሎች መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ፓርኩ የግብርና ምርቶችን በማቀነባበር እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

በአሁኑ ወቅትም ከ750 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ሶስት ባለሃብቶች በቡና፣ በአቮካዶና ማር ማቀነባበርየሚያስችላቸውን የማሽን ተከላ የቁሳቁስና የሰው ሃይል ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጀርመን ቴክኒክ ተራድኦ ድርጅት (ጂ አይ ዜድ) ለሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም የለገሳቸው ሁለት የከባድ እቃ ማንሻ ተሽከርካሪዎች፣ የላቦራቶሪ፣ የስልጠናና የግብይት መሳሪያዎች እንደሚያግዘው አስረድተዋል።

ኢንዱስትሪ ፓርኩን በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ወደ ሥራ ለማስገባትም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በጀርመን ተራድኦ ድርጅት የሥራ ዕድል ፈጠራ  የደቡብ ክልል አስተባባሪ ወይዘሮ ስምረት ስማኖ በበኩላቸው ፓርኩን በማልማት ስራ አጥነትን ለመቀነስ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ወደ ፓርኩ ለሚገቡ ወጣቶች የቴክኖሎጂ፣ የሥራ ክህሎትና ተያያዥነት ያላቸው ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህም ወጣቶችን የሙያ ባለቤት ከማድረግ ባለፈ የሥራ አጥነት  ችግርን ለማቃለል እንደሚረዳ አስተባባሪዋ ተናግረዋል።

ፓርኩ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ እስኪገባ ድረስ የግብዓትና የስልጠና ድጋፍ እንደሚደረግለት አስታውቀዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው ፓርኩ በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሬ ከማምጣት ባለፈ በዞኑ የሚስተዋለውን የሥራ አጥነት ችግር ለማቃለል እንደሚረዳ ገልጸዋል።

ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የግብርና ምርቶች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙና በማቀነባበር ሂደት የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።

ፓርኩን ወደ ሥራ ለማስገባት መንግሥትና የልማት ድርጅቶች እያደረጉት ያለውን ጥረት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው፣ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የዲላ መካከለኛ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የተከናወነው ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መሆኑን ከደቡብ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም