የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

79

ታህሳስ 13 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች ለመከላከያ ሰራዊት ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አመራሮችና ሰራተኞች ድጋፉን ያደረጉት "አለሁ ለወገኔ" በሚል መሪ ሃሳብ ነው፡፡

ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌትነት ታደሰ ድርጅቱ ጋዜጠኞቹን ወደ ግንባር በመላክ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የሰራዊቱን የድል ታሪክ ሰንዶ በማስቀመጥ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በተጨማሪ ሌሎች የአገር ውስጥ የሚዲያ ተቋማትም የሰራዊቱን ተጋድሎ በማሳወቅ ረገድ የሚደነቅ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሰራተኞች በሙያቸው አገራቸውን ከማገልገል ባሻገር ከ3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያነሱት፡፡

በተያያዘ ዜና በአዲስ አበባ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሰናይት አሰሙ ለሰራዊቱ 25 ሺህ ብር የሚያወጣ ሰንጋ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

የወታደር ልጅ እንደሆኑ የሚናገሩት ወይዘሮ ሰናይት አለሙ፤ ድጋፉን ያደረጉት ለሰራዊቱ ያላቸውን አጋርነት ለመግለጽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ የድጋፍና ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አባል ኮሎኔል ሹማ ኦብሳ በበኩላቸው ኀብረተሰቡ እያደረገው ያለው ድጋፍ ሰራዊቱ ግዳጁን በድል እንዲወጣ የሞራል ስንቅ እንደሆነለት ተናግረዋል፡፡

ድጋፉም ኢትዮጵያዊያን ለሰራዊቱ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት የሚገልጽ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም