ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች የሰቆጣ ከተማን ተቆጣጠሩ

89

ታህሳስ 13/2014(ኢዜአ) በአንጸባራቂ ድል ወደፊት እየገሠገሡ የሚገኙት ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች አብዛኞቹን የዋግ ኅምራ አካባቢዎች ነጻ በማውጣት የዞኑን ዋና ከተማ ሰቆጣን ተቆጣጥረዋል፡፡

አካባቢው ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ በሚወጣበት ጊዜ የዋግ ኅምራ ሚሊሻዎች አስደናቂ ጀብዱ የፈጸሙ ሲሆን፣ የአካባቢው ሕዝብም ከመከላከያ ሠራዊትና ከአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመጣመር ደጀንነቱን በብቃት አሳይቷል፡፡

የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይሎች ቀሪዎቹን ሥፍራ እያጸዱ፣ የፈረጠጠውን የአሸባሪውን ጀሌ እየደመሰሱ፣ ወደ አበርገሌ በመገሥገሥ ላይ ይገኛሉ፡፡

በተያያዘም ጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች፣ በቆቦ ግንባር በአንድ በኩል ሙጃና ጥሙጋ ላይ የሠፈረውን የጠላት ኃይል በመጥረግ ወደ አላማጣ ከተማ እየገሰገሰ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተኩለሽን ተቆጣጥረው በማጽዳት፣ ወደ መረዋና ኮረም እየገሠገሡ ይገኛሉ፡፡

በእሳታማው የጀግኖች ክንድ የተደቆሰው አሸባሪው ሕወሐት፣ ተቸካይና ኋላ ቀር በሆነ የጦር ዘይቤ፣ ዕብሪትን እንደ መሣሪያ በመጠቀም፣ ከገባባቸው የአማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች እንደገባ መውጣት አቅቶት፣ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሣራ ደርሶበት ተደምስሷል፡፡

ይሄንን ሐፍረቱን መሸፈን ሲያቅተው በአንድ በኩል ለሰላም ሲል የወጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሽንፈቱ ውኃ የማይቋጥር ምክንያት እያቀረበ፣ አድኑኝ የሚል እሪታ እያሰማ፣ በለመደው ውሸት የትግራይን ሕዝብና የዓለምን ማኅበረሰብ ለማደናገር እየሞከረ ይገኛል፡፡

በዚህ ጦርነት የመጀመሪያው ገፈት ቀማሽ የሆነውና አሸባሪውን ሕወሐት በጀግንነት የታገለው የዋግ ኅምራ ሕዝብ፣ በጀግኖቹ የመከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ የጸጥታ ኃይሎች፣ እንዲሁም በራሱ በዋግ ኅምራ ሕዝብ ትግል፣ ከአሸባሪው ሕወሐት ነጻ በመውጣቱ፣ በዚሁ አጋጣሚ መንግሥት እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት ይወዳል፡፡

ነጻነታችንን የምናስከብረው በተባበረው ክንዳችን ነው!

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም