ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እውነተኛና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እውነተኛና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ
አዲስ አበባ ነሐሴ19/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እውነተኛና ዲሞክራሲያዊ ምርጫን ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስተሩ ከ120 በላይ ከሚሆኑ የአገር ውሰጥ ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ ሲሆን በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ስለመራዘም ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚሁ ጥያቄ ምላሽ "ምርጫው መራዘም የእኔም የድርጅቴም ፍላጎት የለኝም እውነተኛና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ተካሄዶ ማየት ነው ህልሜ" ብለዋል። የአገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከቅርብ ጊዜ በመሆኑ ምርጫው መራዘም እንዳለበት የሚገልጹ ሃሳቦች ከመገናኛ ብዙሃን ተነስተው ነበር። “ያልተመረጠ መሪ ህዝብን ማገልገል የለበትም፤ እኔም የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይመርጠኝ ማገልገል የለብኝም '' ያሉት ዶክተር አብይ ከተመረጡ ብቻ ማገልገል እንደሚፈልጉ ገልጸዋል። የምርጫ ኮረጆ ተሰረቀ የሚል ከመስማት ወጥተን ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ሆኖ በሁሉም ዘንድ በተቃዋሚዎች፣ በህዝብና በኢህዲግ ታማኝ እንዲሆን በቀጣይ የማደራጀት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በህዝቡ፣ በተቃዋሚዎችና በሌሎች አካላትም ምንም ጥርጣሪ ሳይኖር ሁሉም አመኔታ እንዲኖረው ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል። ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሾሙበት ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በኋላ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።