የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በውግንና የሚያካሂደውን እንቅስቃሴ አቁሞ በአማራና አፋር ክልሎች የተካሄዱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር ይኖርበታል

ታህሳስ 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ፖለቲካዊ አጀንዳ በመያዝ በውግንና የሚያካሂደውን እንቅስቃሴ አቁሞ በአማራና አፋር ክልሎች የተካሄዱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር ይኖርበታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታርያት ሀላፊ ቢልለኔ ስዩም በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ባሳለፍነው ሳምንት የተካሄደው የቱርክ አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ውጤታማ እንደነበር አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ የቱርክና አፍሪካ ግንኙነት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ማመልከታቸውንም አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን ኢትዮጵያና ቱርክ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በሚያጠናክሩበት ጉዳዮች ዙሪያ ከቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ጋር መወያየታቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች አብሮ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈጸማቸውን ነው የገለጹት።

በዘመቻ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ወሳኝ የሆኑ ድሎች በአማራና አፋር ክልሎች መገኘታቸውን ያብራሩት ሃላፊዋ አሸባሪው ህወሃት በወራረ ይዟቸው የነበሩ ወልድያን ጨምሮ የሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲወጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

አሸባሪው በወራራ በያዛቸው አካባቢዎች የመንግስት፣ የህዝብና የግለሰብ ተቋማትን ማውደሙንም አመልክተው ከነዚህም መካከል የጤና፣ የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዲሁም የኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ዋና ናቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል አሸባሪው ህወሃት ከወራረቸው አካባቢዎች ለቀው የወጡ ዜጎች ቀስ በቀስ ወደ ቀዬአቸው እየተመለሱ መሆኑንም ገልጸዋል።

በአውሮፓ ህብረት አባል አገራት ጠንሳሽነት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ውሳኔውን ኢትዮጵያ የማትቀበለውና ምንም አይነት ትርጉም የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።

አክለውም አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራትና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገራት ውሳኔ ሀሳቡን መቃወማቸውን አስታውሰዋል።

መንግስት ውሳኔውን አልቀበለውም ያለው የተፈጸሙ ወንጀሎች እንዲመረመሩና ፈጻሚዎቹ ለህግ እንዲቀርቡ ካለመፈለግ ሳይሆን ይልቁንም ጉዳዩ ፖለቲካዊ አጀንዳ ያለው በመሆኑ ነው ብለዋል።

ምክር ቤቱ የሰብአዊ መብትን ጉዳይ ፖለቲካዊ አጀንዳ ከማድረግ ተላቆ በቅድሚያ መንግስት ላከናወናቸው ተግባራት እና በቅረቡ የተካሄደውንም ጥምር የሰብአዊ መብት  ምርመራ እውቅና መስጠት አለበት ብለዋል።

“ምክር ቤቱ በውግንና የሚያካሂደውን እንቅስቃሴ አቁሞ በአማራ ክልልና አፋር ክልል የተካሄዱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር ይኖርበታል” ሲሉም ገልጸዋል።

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም