አቶ ካሳሁን እምቢአለ የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ

109

ደብረ ብርሃን ታህሳስ 12/2014 (ኢዜአ) የደብረ ብርሃን ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ ካሳሁን እምቢአለን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በማድረግ ሹመት ሰጠ ።

 በጉባኤው የከተማውን የ2014 በጀትም ምክር ቤቱ አፅድቋል።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ መንግስቱ ቤተ በወቅቱ እንደገለፁት አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ላይ በከፈተው የውክልና ጦርነት ከፍተኛ የሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

የከተማው ህዝብ የህልውና ዘመቻውን በመደገፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስግነው፤ ነዋሪዎች አሁን ላይ በተገኘው አንፃራዊ ሰላም በመጠቀም የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሌላ በኩል የደብረ ብርሃን ከተማ ምክር ቤት አቶ ካሳሁን እምቢአለን  የደብረ ብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በማድረግ ሾሟል።

አቶ ካሳሁን እምቢአለ ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር በመንግስትና ህዝብ የተጣለባቸውን አደራ በብቃት እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅና የከተማውን እድገት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት ህብረተሰቡ የነቃ ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ምክር ቤቱ  የከተማውን ህዝብ  በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ  የ2014 ዓመት መደበኛና የካፒታል በጀት 621 ሚሊየን 641 ሺህ 246 ብር መርምሮ አፅድቋል።

ምክር ቤቱ የከተማውንየቀጣይ የልማት፣ የሰላም፣ የህግ ማስከበርና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ ለሚከናወኑ ስራዎች አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉባኤውን አጠናቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም